የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፦ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት እና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያዎችን ለማድረግ ፍላጎት ካሳየ የጃፓን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቡድን ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡
ቡድኑ እንደ ፓናሶኒክ እና ቶዮታ ካሉ ዕውቅ የጃፓን አለም አቀፍ አምራች ኩባንያዎች እና በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርገው በመስራት ላይ ከሚገኙ እንደ ዶዳይ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል አምራች ኩባንያዎች ያሉ ተቋማት የተውጣጣ መሆኑ ተገልጿል።
ቡድኑ በተለይም በኢንሹራንስ፣ ኤሌክትሮኒክ እና አይ ሲ ቲ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና የሶፍትዌር ኢንቨስትመንት ዘርፎች እና ሌሎችም ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቋል።
ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ቡድኑ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ያሳዩትን ፍላጎት አድንቀው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመት ከባቢ ያሉ ዕድል እና አማራጮች እንደዚሁም የተደረጉ የህግ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ ለቡድኑ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑ ለሚኖሩት ኢንቨስትመንት ተኮር ፕሮጀክቶች ኮሚሽኑ ሙሉ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው መረጃ አመላክቷል።