የኢድ አል ፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት ተጠናቋል - የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ አል ፈጥር በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት ተጠናቋል - የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 1/2016(ኢዜአ)፡- ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲያከብር በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ተግባር መግባቱን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
ግብረ ሃይሉ ባወጣው መግለጫ ሰላም ወዳዱ የሀገራችን ሕዝብ ለሰላምና ደኅንነት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ በሚካሄደው የፀጥታ ማስከበር ሥራ ውስጥ በባለቤትነት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ገልጿል፡፡
ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ከጋራ ግብረ-ኃይሉ ጎን ሆኖ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል።
ግብረ ሃይሉ በመግለጫው የሀገርን እና የህዝብን ጥቅም አስቀድማችሁ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ በማበርከት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየሠራችሁ ላላችሁ በግዳጅ ላይ ለምትገኙ የፀጥታ አካላት አመራር እና አባላት ግብረ-ኃይሉ የላቀ ምስጋና ያቀርባል ማለቱን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡