ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን- አቶ ይርጋ ሲሳይ - ኢዜአ አማርኛ
ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን- አቶ ይርጋ ሲሳይ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 01/2016 (ኢዜአ)፡- ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።
አቶ ይርጋ ሲሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎችን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል።
እንደክልል ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም ፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት፣ ተግዳሮቶች ወደ ስኬት በመቀየር፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን።
ሀገራዊ ለውጡን የወለደው የብልጽግና ፓርቲ የሀገራችንን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው አገራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክርና በወንድማማችነት/በእህትማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ በማየት ሁሉን አቀፍና ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል በፅኑ ያምናል። ስለዚህ አገራዊ አንድነታችን በሕግ፣ በአሠራርና በተቋም ደረጃ ዋና አጀንዳ በማድረግ እየሠራን እንገኛለን።
ይሁን እንጅ በክልላችን ጽንፈኝነት የወለደውን አስተሳሰብ የሚጋሩ አካላት የክልላችን ህዝብ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ታግሎ ያመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ ብሎም ክልሉን ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቻችንና ሰላምን ከማይፈልጉ የውስጥና የውጭ አካላት ጋር በመናበብ እኩይ ተግባር ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ መላ የክልላችን ህዝብ በማሳተፍ በክልላችን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የጽንፈኞችን እኩይ ተግባር ለማክሸፍ በየደረጃው የሚገኝ አመራርና ህዝቡ እንዲሁም ጀግናው መከላከያ ሃይላችን በከፈለው መስዋዕትነት የሴረኞችና ጽንፈኛ ሃይሎችን ከንቱ ህልም ማክሸፍ ተችሏል፡፡
በመሆኑም በፓርቲያችን ሊቀመንበር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብልፅግና የማይቀር መሆኑን ያረጋገጡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ድሎችን አስመዝግበናል። በክልላችንም ውስጥ ትልቅ የብልጽግና አሻራ መተከሉን በርካታ የክልላችን ከተሞች ድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
በቀጣይም ምንም እንኳ በጉዟችን መሀል እንደክልል ሰው ሰራሽ እና ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም ፣ ፈተናዎችን ወደ እድል ቀይረን፣ አቅማችንን ወደ ውጤት፣ ተግዳሮቶች ወደ ስኬት በመቀየር፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ጉዟችንን ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ እንቀጥላለን።
በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችም አንድነታችንን በማጠናከር ፅንፈኝነትን፣ ውጤታማ አለመሆንን፣ ሌብነትን እና ሙስናን በመታገል ፈታኝ የሆነውን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በክልላዊ ኮንፈረናሳችን የገባነውን ቃል እውን እናደርጋለን።
በዚህ ሂደት የክልላችን ነዋሪዎች ከጎናችን መሆናችውን በህዝባዊ ማዕበል በታጀበ ሰልፍ አረጋግጣችሁልናልና ለሰጣችሁን እውቅና የላቀ ክብርና ምስጋና አለን።
በቀጣይም በክልላችን ዘላቂ ሰላምን በማጽናት ሁለንተናዊ ለውጥን ለማረጋጥ ህዝቡ ጋር ተቀራርበን ለመስራት የምንንቀሳቀስ ሲሆን ለዴሞክራሲ መጠናከር የማይተካ ሚና ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት ለክልላችን ለኢትዮጵያችንና ለህዝቦቿ ብልፅግና በጋራ እንድንሰራ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አመሰግናለሁ!!