ቀጥታ፡

ሀገር ወዳድ የሆነ ምሁር ተቋም ያሻግራል፤ ሀገር ይገነባል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በጥራት ፣ በብቃትና በልምድ ተመራጭ የሆነ ሃይል በማፍራት የመከላከያን ተልዕኮ በፍጥነትና በውጤት ማሳለጥ የሚችል ተቋም ነው ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ኤታማዦር ሹሙ የሠራዊቱን የውጊያ አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ ያለቀላቸው የምርምር ስራዎችን በዩኒቨርሲቲው ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም ላይ ሀገር ወዳድ የሆነ ምሁር ተቋም ያሻግራል ሀገር ይገነባል ያሉት ኤታማዦር ሹሙ አዳዲስ የምርምር ግኝቶችን ፈጥሮ በመስራት የመከላከያ ሠራዊታችንን የትጥቅ አቅም በዘመናዊ ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ውጤት የታገዘ እንዲሆን በትኩረት መማርና መመራመር ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል ።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በጥራት በብቃትና በልምድ ተመራጭ የሆነ ሃይል በማፍራት የመከላከያን ተልዕኮ እያሳለጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመከላከያ ሰራዊቱን ውስብስብ የግዳጅ ጉዞዎች ቀላልና ምቹ ማድረግ የሚችሉ የምርምር ሥራዎችን በመስራት ያበረከተውን አስተዋፅኦም አድንቀዋል።

በዘላቂ ጥናትና ምርምር የላቀ ውጤት በማምጣት ኢትዮጵያ በወታደራዊ ትጥቆች እራሷን እንድትችል የተገኙ የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርት ማስገባት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ተቋሙ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚችል አቃፊና ተፈላጊ ተቋም እንዲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፣የቦርድ አባላት ፣መምህራን እና ተመራማሪዎች በትብብር እንዲሰሩም ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም