ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በንብረት አያያዝ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በአፋጣኝ እንዲያርም አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በንብረት አያያዝ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በአፋጣኝ እንዲያርም አሳሰበ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በንብረት አያያዝ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በአፋጣኝ እንዲያርም አሳሰበ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ 2014/15 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ፕሮጀክት አፈጻጸም ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ፕሮጀክትን ለማስፈጸም የሚያስችሉ 18 መመሪያዎች እና የአሰራር ማኑዋሎች አለመጽደቃቸውን አንስተዋል።
የአዋጭነት ጥናት እና ንድፍ ያልተከናወነባቸው ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸው እና ፕሮጀክትን በተያዘለት በጀት እና ጊዜ በማጠናቀቅ በኩል ጉድለቶች ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል።
ለፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች በውል መሰረት አለመቅረብ እና የግብአቶች መከማቸት እና ከግንባታ የሚተርፉ ግብአቶች ብክነት እንደሚስተዋልም ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተናገሩት።
የኃይል ብክነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርአት አለመዘርጋቱ እና ግንዛቤ የሚሰጥበት ስርአት እየተተገበረ አለመሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በእቅድ ላይ የተመሰረተ ስራ ባለመስራቱም በቢልዮን የሚቆጠር ሀብት ማጣቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ መመሪያዎች እና ማኑዋሎች አለም አቀፍ ህጎችን መሰረት አድርገው በተቋሙ መዘጋጀታቸውን አንስተው፥ በቦርድ እንደሚጸድቁ ገልጸዋል።
ለእያንዳንዱ ፕሮጀክቶች የሚወጡ የፋይናንስ ወጭዎች በአግባቡ በዲጂታል ስርዓት እየተመዘገቡ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ ግንባታቸው ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ችግር ለመቅረፍም መልሶ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከግንባታ የሚተርፉ ግብአቶች የሚባክኑበትን ሁኔታ ለመቅረፍ በተለያዩ አካባቢዎች የመጋዘን ግንባታ እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው፥ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ መኖራቸውን ገልጸዋል።
ቅንጅታዊ አሰራርን ከማስፈን አኳያ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት በጅምር ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚከናወኑ ስራዎች ለሌሎች የልማት ስራዎች መሰረት በመሆናቸው በጸደቁ መመሪያዎች እና ማኑዋሎች መመራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በቂ የሆነ ፋይናንስ ሳይያዝ ፕሮጀክቶች መጀመር እንደሌለባቸው እና ይህም የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ ለመከላከል እንደሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከግንባታ የሚተርፉ ግብአቶችን በአግባቡ በማደራጀት ለሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲውሉ ማድረግ አና ብክነት ቆጣቢ የሆነ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ተቋሙ በንብረት አያያዝ ላይ እየተስተዋሉበት ያሉ ችግሮች ላይ አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር የሺመቤት ደምሴ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የሆነ የንብረት ብክነት መኖሩን ገልጸዋል።
ይህም በአፋጣኝ መታረም ያለበት መሆኑን ገለጸው በየቦታው በርካታ ገንዘብ የወጣበት ሀብት መባከን እንደሌለበት አሳስበዋል።
ተቋሙ እነዚህን ንብረቶች ለማስቀመጥ የጀመረው የመጋዘን ስራ መልካም መሆኑን ገልጸው በየዲስትሪክቱ ማስፋፋት እንዳለበት አመላክተዋል።
በቀጣይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አሰራሮችን በመፈተሽ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባ እንደሚገባ ገልጸዋል።