ቀጥታ፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ በድጎማ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ተመዝግቦ የነበረውን የ197 ቢሊየን ብር ዕዳ ወደ 92 ቢሊየን ብር ዝቅ እንዲል አድርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ በድጎማ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ተመዝግቦ የነበረውን የ197 ቢሊየን ብር ዕዳ ወደ 92 ቢሊየን ብር ዝቅ እንዲል ማድረጉን የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።

በባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከ2014 ዓ.ም በፊት ሁሉም የተሽከርካሪ ዓይነቶች የጥቅል ድጎማ ተጠቃሚ ነበሩ ። 

በፖሊሲ የተደገፈ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ባለመዘርጋቱም በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አማካኝነት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ መሸጫ ባነሰ ዋጋ ሲቀርብ እንደነበር ተናግረዋል።

ይህ በመሆኑም በነዳጅ ማረጋጊያ ተቀማጭ ገንዘብ አልቆ ዕዳ እንዲመዘገብ በማድረግ ነዳጅን ከውጭ ገዝቶ ለማስገባት ወደ ማይቻልበት ፈታኝ ደረጃ ተደርሶ እንደነበር ጠቁመዋል።

ወደ ሕብረተሰቡ መተላለፍ ያለበት ዋጋ ባለመተላለፉም የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ በጀት አልቆ በአንድ ወር ብቻ ከ10 እስከ 15 ቢሊየን ብር ዕዳ መመዝገብ ጀምሮ እንደነበር አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብና የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ መሆን ለሀገር ጥቅም ሳይውል በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ጎረቤት ሀገራት በኮንትሮባንድ ጭምር እንዲሸጥ አድርጎት ነበር ብለዋል።   

በዚህ መነሻነትም በጥናት ላይ የተመሠረተ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ተቀማጭ ድጎማ ፈንድና የኮንትሮባንድ ጫናን መቀነስ የሚያስችል የድጎማ ማሻሻያ እርምጃ እንደተወሰደ ገልፀዋል።


 

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ላይ የተወሰደው እርምጃ ዕዳን በመቀነስ፣ ኮንትሮባንድን በማስቀረት፣ የነዳጅ አቅርቦቱ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር በማድረግ ገንቢ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል። 

የነዳጅ ዋጋ በሚቀንስበት ወቅት የተመዘገበውን ዕዳ ማቃለል እየተደረገ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ከነዳጅ ድጎማ ስላልተወጣ አሁን ላይ ጭምር አነስተኛ ዕዳ እንደሚመዘገብ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት የተመዘገበውን የ197 ቢሊየን ብር ወደ 92 ቢሊየን ብር ዝቅ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።

በድጎማ ሥርዓት የቆየውን የነዳጅ ዋጋም የጊዜ ገድብ በማስቀመጥ መደጎም ያለበትና የሌለበት ተሽከርካሪ ተለይቶ በሂደት ከድጎማ የሚወጣበት አሠራር ተቀምጦ እየተሰራበት ነው ብለዋል። 

በተዘረጋው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የአሠራር ሥርዓትም ከከተማ አውቶቡስና ታክሲ ውጭ የሆኑ ተሽከርካሪዎች በአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ከድጎማ መውጣታቸውን አስታውቀዋል። 

የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስና ታክሲ በታለመለት የነዳጅ ድጎማ እንዲገቡ በማድረግ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ጫና እንዳይበዛበት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገበት ሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ28 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለአሽከርካሪዎች ድጎማ መደረጉን ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራትም 12 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የገንዘብ ክፍያ ለተሽከርካሪዎች እንዲፈጸም መደረጉን ተናግረዋል። 

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሙሉ በሙሉ አይወጣም ያሉት ዳይሬክተሯ፤ መጀመሪያ የ25 ሊትር ድጎማ ከተደረገለት በወራት ልዩነት ወደ 19፣ 12 እና 3 ሊትር ዝቅ እንዲል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ አውቶቡሶችና ታክሲዎችም በሂደት ከድጎማ ሥርዓቱ እንዲወጡ ይደረጋል እንጂ አሁን ላይ መንግሥት ድጎማውን ሙሉ በሙሉ ያነሳበት ሁኔታ እንደሌለ አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት በማደያዎች ላይ የነበረው የተሽከርካሪ መጨናነቅና የተወሰነ የነዳጅ እጥረትም በጅቡቲ የጣለው ከባድ ዝናብ የመንገድ ብልሽት በማስከተሉ እንደሆነ ገልፀዋል።

በተከናወነ የተቀናጀ የመፍትሔ እርምጃም 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ሊትር ነዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንዲሰራጭ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በቀጣይም በኢትዮ-ቴሌኮም ትብብር በቴክኖሎጂ የታገዘ "የፊውል ማኔጅመንት ሲስተም" በመዘርጋት ፍትሃዊ የነዳጅ ቁጥጥርና ሥርጭት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለአካባቢ ምቹ የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረጉም የነዳጅ ጥገኝነት በመቀነስ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወቱ አንስተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም