የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገትን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስመዘግበውን ተጨባጭ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የደንበኞች አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1946 መጋቢት 29 በአሥመራ በኩል በማድረግ ወደ ግብጽ ካይሮ በ/5C-47/ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተበትን 78ኛ ዓመት አስመልክቶ የመጀመሪያ በረራውን ወዳደረገበት ካይሮ ትላንት ማታ በልዩ ዝግጅት በረራ አድርጓል። 

በትላንትናው ዕለትም አየር መንገዱ የ78 ዓመታት የስኬት ጉዞውን አስመልክቶ ባደረገው በረራ  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በረራው ላይ ተጓዥ ለነበሩ ደንበኞች አገልግሎት ሰጥተዋል።  


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ያስመዘገበውን የስኬት ዓመታት ለማክበር ይህ ጉዞ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

አየር መንገዱ በጥቂት አውሮፕላን ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፤ አሁን ላይ አጠቃላይ አቅሙን በማሳደግ በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም አቀፍ ደረጃም ስመጥር አየር መንገድ መሆን ችሏል ነው ያሉት።

አየር መንገዱ ከሰባት አሥርት ዓመታት በላይ በነበረው ጉዞው ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ያስቻለው የማይለዋወጥ ወጥ አቋም በመያዝ በትጋት በመሥራቱ ነው ሲሉም ተናግረዋል።  

አየር መንገዱ ስኬታማ ሆኖ የመቀጠሉ አንዱ ምስጢር ለደንበኞች የሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም እድገቱን ለማስቀጠል የደንበኞች አገልግሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

በልዩ በረራ ላይም አየር መንገዱ ለደንበኞቹ የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማስቻል ለተጓዞች በአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል። 


 

የዕለቱ ታሪካዊ ጉዞ ዋና አብራሪና የአየር መንገዱ የበረራ ክፍል ምክትል ፕሬዝዳንት ካፒቴን ዮሴፍ ኃይሉ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ሁልጊዜም ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር ጥረት የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል። 

በተለይ የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታ ለማስጠበቅ በአየር መንገዱ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን በማንሳት በዛሬው ዕለትም የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ይህንኑ ለማሳየት አገልግሎት መስጠታቸው የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

በበረራው ተጓዥ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት መንገደኞች በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው አፍሪካውያን ኩራት ሆኗል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ላይ በመገኘት በአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች የተደረገላቸው መስተንግዶ ያስደሰታቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ የጀመረውን እድገቱን ማስቀጠል ላይ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከተቀላቀለ ጊዜ አንስቶ  በአህጉሪቷ የመጀመሪያ የሆኑትን የጀት ምርቶች በማስገባት ቀዳሚ ሲሆን፤ የመጀመሪያዎቹን የ/B767/፣ /B777-200LR/፣ /B787/ ድሪም ላይነር እና የ/787-9/ አውሮፕላኖችን በቀዳሚነት ወደ ገበያው ያስገባ መሆኑ ይታወቃል።

ዛሬ ላይ አየር መንገዱ ባሉት 147 አውሮፕላኖች ከ136 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዬን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

አየር መንገዱ ያኔ የመጀመሪያውን በረራ ያደረገባት የካይሮ ከተማም ዛሬ ላይ አየር መንገዱ በየቀኑ ከሚበርባቸው የአፍሪካ ከተሞች አንዷ ናት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም