በደሴ ከተማ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት ዘላቂ ልማትና ሰላም ማረጋገጥ ችለናል - ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት ዘላቂ ልማትና ሰላም ማረጋገጥ ችለናል - ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ

ደሴ ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ ባለፉት ዓመታት የለውጡ አመራር ከህዝብ ጋር በመወያየትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በመለየት በቅንጅት በመስራቱ ውጤት ማስመዝገቡን የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።
በለውጡ አመራር በርካታ የልማት ስራዎች በመከናወናቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እየመለሱ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በለውጡ የተገኙትን ስኬቶችና የልማት ውጤቶች በመደገፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፤ የለውጡ አመራር ከህዝብ ጋር በመወያየት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በመለየት በቅንጅት በማከናወኑ ውጤት አስመዝግቧል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በከተማው ዘላቂ ልማትና ሰላም ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡
ለመልካም አስተዳደር ችግሮችም የተደራጀ መፍትሄ በመስጠት በከተማው የመንገድ፣ የትምህርት፤ የጤናና የሌሎችም መሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም 10 የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የለውጡ መንግስት የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሌሎች አገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን "በጥራት ማጠናቀቅ እንደሚችልም በተግባር አረጋግጧል" ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ አገር የሚያፈርሱ፣ ልማት የሚያወድሙ፣ አንድነታችንን የሚሸረሽሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን ከመንግስት ጋር መታገል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በተለይ አማራ ክልልን በውክልና ጦርነት ህብረተሰቡን ለእንግልት እየዳረጉ የሚገኙ ጽንፈኞችን በቃችሁ ማለትና "ዘላቂ ሰላም መፍጠር ከሁላችንም ይጠበቃል" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ የለውጡ አመራር በደሴ ከተማ በርካታ ልማቶችን በመስራት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በየደረጃው እየመለሰ መሆኑን አመልክተዋል።
የሰልፉ ተሳታፊ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ እንደተናገሩት፤ የለውጡ አመራር በደሴ ከተማ የልማት ተግባራትን በማከናወን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው።
እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በየደረጃው በመመለሰ ለህዝብ የገባውን ቃል እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ እርሳቸውም ከመንግስ ጎን ሆነው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የለውጡ መንግስት ህብረ ብሔራዊነታችን እንዲጠናከር ከማድረጉ ባለፈ በተሰሩ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል ለቀጣይነቱም የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።
ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ፋኢዛ ካሳው በበኩላቸው፤ በከተማችን ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም የተጀመረው ለውጥ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳርና በደቡብ ወሎ ዞንን ከ10 ወረዳዎች በሚበልጡ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፉ ተካሂዷል፡፡