ሀገራዊ ለውጡ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የተረጋገጠበት ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የተረጋገጠበት ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ እኩልነትና እውነተኛ ፌዴራሊዝም የተረጋገጠበት መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
በሀዋሳ ከተማ ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የመጣው ለውጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ ጉዞዎች በህዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን በመመለስ በርካታ ድሎችና ትሩፋቶችን አስገኝቷል ብለዋል።
አንዱን ቤተኛ ሌላውን የዳር ተመልካች አድርጎት የነበረው ተለውጦ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና እውነተኛ ፌዴራላዊ የተረጋገጠባት እንደሆነች ተናግረዋል።
የለውጡ ዓመታት በተለይ ሲዳማ ለዘመናት ሲታገልለት የነበረውን እራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ የተመለሰበት እንደሆነ አውስተዋል።
ይህንን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚጥሩ በክልሉ ህዝብና መንግስት በፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለይ በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ በመምጣት ህዝብ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አንስተው፤ ከዚህም በስንዴ ምርት የተገኘው ስኬት ለአብነት ጠቅሰዋል።
በለውጡ መንግስት በሳል አመራርና በላቀ ትኩረት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የፍፃሜ ምዕራፍ ማድረስ የተቻለበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ ለውጡን ቀጣይነት እንዲኖረው የአካባቢውን ሠላም እንዲያስጠብቅና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል የጎርቼ ወረዳ ነዋሪ አቶ ታምሩ ሪቂባ፤ የለውጡ መንግስት በአካባቢያቸው ያስገኘውን የልማትና ሌሎች ትሩፋቶችን በመደገፍ ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ጥያቄዎቻችን ተመልሰውልናል ያሉት አቶ ታምሩ፤ በወረዳቸው የመንገድ፣ የመብራትና ሌሎች የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘማች ኢርጢባ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግስት ተቀዛቅዞ የነበረውን የህዳሴ ግድባችንን ሥራ ዳግም በማስጀመር ትልቅ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው ብለዋል።
በአካባቢያቸው ሰፋፊ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ይህ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው በየአካባቢያችን ለሠላማችን ባለቤት ሆነን መስራት ይጠበቅብናል ያሉት አቶ ዘማች፤ ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።
በድጋፍ ሰልፉ የሀዋሳ ከተማና የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።