የኢድ አል ፈጥር በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በመደገፍና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል - የእምነቱ ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ አል ፈጥር በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በመደገፍና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን ይገባል - የእምነቱ ተከታዮች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016 (ኢዜአ)፦ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በመደገፍና የተቸገሩትን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች ገለጹ፡፡
የዘንድሮው የኢድ አል ፈጥር በአል ጨረቃ ከታየች ማክሰኞ ካልታየች ደግሞ ረቡዕ እንደሚከበር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መግለጹ ይታወሳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች እንዳሉት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ከአቅመ ደካሞች እና ከተቸገሩ ሰዎች ጋር ያለውን በማካፈል መሆን አለበት።
በኢትዮጵያዊ ባህል አብሮ መብላት የቀደመ መስተጋብር በመሆኑ በዓሉን በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት በጋራ ማክበር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በእምነቱ አስተምህሮ መሰረት ህዝበ ሙስሊሙ ከመፆምና ከመስገድ ባሻገር ወሩን ሙሉ የተቸገሩትን በመርዳትና በጎ ስራዎችን አብዝቶ በመተግበር እንደሚያሳልፍ ጠቅሰዋል።
በዓሉ በዋናነት ፈጣሪን የምናመሰግንበትና የሰራናቸውን ስራዎች እንዲቀበለን የምንማጸንበት ነው ብለዋል።
አቅመ ደካሞች በዓሉን ተከፍተው እንዳያሳልፉ ዘካ ተል ፊጥር ወይም የትዕዛዝ የበዓል አስራት በማውጣት ሁሉም ሰው እኩል የኢል ደስታ እንዲያገኝ የሚደርግበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የደግነት ሥርዓት በማድረግ በአሉን ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ካነጋገርናቸው የእምነቱ ተከታዮች መካከል ወይዘሮ ሂሩት ሸዋንግዛው እንዳሉት፤ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት "ዘካተል ፊጥር" በመስጠት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በኢድ አል ፈጥር በአል የተቸገሩ ጎረቤቶችን በመርዳትና ካላቸው በማካፈል በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ መሬማ ያሲን በበኩላቸው በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደመቀ መልኩ ከማሳለፍ ባለፈ በመረዳዳት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
ሌላው የእምነቱ ተከታይ ካሚል ናስሮ በበኩሉ፤ በአሉን ስናከብር ጧሪ የሌላቸውንና አቅመ ደካማ ወገኖችን በመጠየቅና ካለን በማካፈል ሃይማኖታዊ ትዕዛዙን መፈጸም ይገባናል ብለዋል፡፡
በችግር ውስጥ ያሉ ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች በመጎብኘትና ካለው በማካፈል በዓሉን ለማክበር መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡
በአሉ ከቤተሰብ እና ከዘመድጋር በመሰባሰብ የሚከበር በመሆኑ በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀቷን የተናገረችው ደግሞ ሃናን ሙሃመድ ናት፡፡