ቀጥታ፡

በአካባቢያችን የተጀመሩ አበረታች የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ  የበኩላችንን እንወጣለን -  የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች 

መተማ ፤  መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፡- መንግስት በአካባቢያቸው የጀመራቸው አበረታች  የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ  የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። 

በዞኑ ገንዳ ውሃ ከተማ ባለፉት ስድስት ዓመታት የመጡ ለውጦችን የሚደግፍ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።

በሰልፉ ስነ-ስርዓት ላይ ከተሳተፉት የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በቀለ ጀመረ በሰጡት አስተያየት፤በለውጡ መንግስት የተጀመሩ የልማት ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከመንግስት ጎን ሆነው ሰላም የማስክበር ስራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያግዙ ገልጸዋል።

ሌላኛው በመተማ ወረዳ አጋም ውኃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ አዲሱ እንዳሉት፤ ሰላምን ለማፅናት ከመንግሥት በተጨማሪ ህዝቡ ኃላፊነት ወስዶ መስራት ይኖርበታል።

የለውጡ መንግስት ሰላምን ከማረጋገጥ ባሻገር የተጀመራቸው አበረታች የልማት ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጠል የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሃመድ ፤ የከተማውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በለውጡ መንግስት የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባ አመልከተዋል።

በከተማዋ ዙሪያ የሚታዩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴያዎችን ለማስቆም ከፀጥታ ኃይሉ ባሻገር የህዝቡ ሚና የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመንደፍና ሰርቶ በማጠናቀቅ  እየተገበረ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ናቸው።

ሰላምንና ልማትን ለማደናቀፍ የሚሞክረውን ፅንፈኛ ቡድን ሀዝቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ በመታገል  የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሰልፈኞቹ በጥቂት ፅንፈኛ አስተሳሰብና እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገርና ህዝብ የለንም፣ የላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም