ቀጥታ፡

ለክልላችን ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣለን - የሐራ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ ለክልላችን ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሐራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

“ለክልላችን ሰላም በህብረት እንቆማለን" በሚል መሪ ቃል በሐራ ከተማ አስተዳደር የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

የድጋፍ ሰልፉ ባለፋት 6 ዓመታት በለውጡ መንግሥት የመጡትን የማህበራዊ ፖሊቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በለውጡ ዓመታት ላሳየው እመርታ ድጋፍ ለመግለጽ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሰልፈኞቹ በማህበራዊ ዘርፍም ሥራ አጦችን በውጭ ሀገራት ሳይቀር በማሰማራት ሥራ እንዲያገኙና በሚሄዱባቸው ሀገራት ክብር እንዲያገኙ የተጀመረው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል ።

በፖለቲካው ረገድ መንግሥት በሀገሪቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን በብልሃት ለመፍታት የሄደበት ርቀት የበሰለ ፖለቲካ በሀገራችን እየዳበረ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ሰልፈኞቹ "እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣለን፣ በጥቂት ፅንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰብ እና እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገርና ህዝብ የለንም፣ ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማሻገር ከለውጡ አመራር ጋር በፅናት እንቆማለ" በማለት ባስተላለፏቸው መልእክቶች ድጋፋቸውን ገለጸዋል።

በተጨማሪም "ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የታደገ እና ህልውናችንን ማስቀጠል ያስቻለ ነው፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬችን መገለጫ ነው፣ ክልላችንን በውክልና ጦርነት ማፍረስ አይቻልም፣ ውስጣዊ ሠላማችንን በማፅናት ውጫዊ ተፅዕኖዎችን በድል እንወጣለን፣ የክልላችንን አንፃራዊ ሠላም በአጭር ጊዜ ወደ ዘላቂ ሠላም እናሸጋግረዋለን የሚሉ" እና ሌሎች መልዕክቶች ማስተላለፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም