ቀጥታ፡

ለክልላችን ሰላም በህብረት እንቆማለን - የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦ለክልላችን ሰላም በህብረት እንቆማለን ሲሉ ባለፉት 6 ዓመታት ለውጡን ተከትሎ ለተገኙ ስኬቶች እውቅና ለመስጠት ለህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ የወጡ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በደሴ ከተማ እየተካሄደ ያለው ሰልፍ "ለክልላችን ሰላም በህብረት ዕንቆማለን " በሚል መሪ ሀሳብ ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩላችንን እንወጣለን፣ በጥቂት ፅንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰብና እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገርና ህዝብ የለንም፣ የላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልፅግና፣ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማሻገር ከለውጡ አመራር ጋር በፅናት እንቆማለን፣ የሚሉ መልዕክቶችን የሰልፉ ተሳታፊዎች አስተላልፈዋል።


 

ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የታደገና ህልውናችንን ማስቀጠል ያስቻለ ነው፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው፣በጠላቶቻችን የቆየ ሴራና በተላላኪዎች ድንፋታ የብልፅግና ጉዟችን አይደናቀፍም፣ ኢትዮጵያ የአድዋን ድል ዳግም እያደሰች ነው፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድልና ስኬት የአባቶቻችንን ገድል የደገምንበት ታሪካዊ አሻራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ታሪካዊ ቀን ናት፣ ያሰበውን የሚሠራ የጀመረውን የሚጨርስ መንግስት አለን፣ ሠላማችን በእያንዳንዳችን ቤት ናት፣ለሀገራችን ሠላምና አንድነት የማንከፍለው ዋጋ አይኖረንም፣ክልላችንን በውክልና ጦርነት ማፍረስ አይቻልም፣ የክልላችንን አንፃራዊ ሠላም በአጭር ጊዜ ወደ ዘላቂ ሠላም እናሸጋግረዋለን የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችም እየተላለፉ ነው።

ህብረተሰቡ ከማለዳው ጀምሮ ከገጠር ቀበሌዎች ጭምር ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሆጤ ስታዲየም እየተሰባሰበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም