ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ

ሰቆጣ/ደሴ/መተማ/ጎንደር፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የለውጡ ውጤቶች ተጠናክረው አንዲቀጥሉ የሚደግፉ ህዝባዊ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። 

የድጋፍ ሰልፉ እየተካሄደባቸው ካሉት የክልሉ አካባቢዎች መካከል ደሴ ሰቆጣና መተማ ከተሞች ይገኙበታል።

እንዲሁም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 7 ወረዳዎች የድጋፍ ሰልፉ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ የኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ምህረት ለኢዜአ ገልጸዋል።


 

በዞኑ የድጋፍ ሰልፉ እያካሄዱ ካሉ ወረዳዎች  ውስጥ  ጭልጋ፣ አይከል፣ ምዕራብ በለሳ፣ ኪንፋዝ፣ መሃል አርማጭሆና ላይ አርማጭሆ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡

ሰልፈኞቹ  "እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአገራችን ሰላምና ብልፅግና የበኩላችንን ሚና እንወጣለን፣ አገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የታደገና ህልውናችንን ማስቀጠል ያስቻለ ነው፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው " የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።


 

እንዲሁም "ሰላማችን በእያንዳንዳችን ቤት ናት፣ የላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልፅግናና፣ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ታሪካዊ ቀን ናት፣ ያሰበውን የሚሰራ የጀመረውን የሚጨርስ መንግስት አለን፣ ለአገራችን ሰላምና አንድነት የማንከፍለው ዋጋ አይኖረንም፣ ውስጣዊ ሰላማችንን በማፅናት ውጫዊ ተፅዕኖዎችን በድል እንወጣለን፣ የሚሉም እንዲሁ። 

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ባሉት ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ሴቶች፣ ወጣቶች ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም