በሞዛምቢክ በደረሰ የጀልባ አደጋ ህጻናትን ጨምሮ ከ90 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ

2128

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦በሞዛምቢክ ሰሜናዊ ክፍል የባህር ዳርቻ በተከሰተ የጀልባ አደጋ ህጻናትን ጨምሮ ከ90 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።

በሞዛምቢክ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ናምፑላ ግዛት 130 የሚሆኑ ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ መስጠሟን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ነዋሪዎቹ በግዛቷ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ በመሸሽ ወደ ሌላ አካበቢ ለመሄድ በጀልባ በተሳፈሩበት ወቅት አደጋው እንደተከሰተ የገለጹት ባለስልጣናቱ ጀልባዋ መሸከም ከምትችለው የሰው መጠን በላይ በመጫኗ አደጋው እንደደረሰ አመልክተዋል።

በዚህም ህጻናትን ጨምሮ ከ90 በላይ ሰዎች ሕይታቸው እንዳለፈ ማረጋገጣቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት አምስት ሰዎችን ከአደጋው በሕይወት ማትረፍ እንደተቻለ ያመለከተው ዘገባው ተጨማሪ ሰዎችን ለማዳን ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስነብቧል።

የናምፑላ ግዛት ባለፈው አመት በሞዛምቢክ በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱ አካባቢዎች መካከል አንዷ መሆኗም በዘገባው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም