ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተፈፀመ ስርቆት 22 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ወድቀዋል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተፈፀመ ስርቆት 22 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ወድቀዋል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2016(ኢዜአ)፦የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የስርቆት ወንጀሉን ለመከላከል መንግስትና በየደረጃው የሚገኙ አካላት በመቀናጀት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ እንዳስታወቀው የስርቆት ችግሩ ከመደበኛ ሥራቸው ይልቅ በአስቸኳይ የጥገና ሥራዎች ላይ ለማተኮር አስገድዷል።
በዘርፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና የሪጂን ማስተባበሪያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ሪጂኖች በሚገኙ የኃይል ማስተላለፈያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ስርቆት ተፈፅሟል።
በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ሽቦ ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት 22 ምሰሶዎች መውደቃቸውንና ከዚህ ውስጥ ሰባቱ በሰሜን ምዕራብ ሪጂን በተፈፀመ ስርቆት የወደቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አስር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን ፈታትቶ ለመውሰድ በተፈፀመ ከፍተኛ ስርቆት ምክንያት በጊዜያዊነት ኃይል ማስተላለፍ አቋርጠው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በስርቆት ምክንያት ከወደቁ ምስሶዎች በተጨማሪ ከመሬት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዙና በሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ደግሞ 13 ምሰሶዎች መውደቃቸውንም አስታውቀዋል።
በዘርፉ የሪጂን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተሮች እንደገለፁት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎች አየተከናወኑ ቢሆንም እየተባባሰ የመጣው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች አካላት ስርቆት በኦፕሬሽን ሥራው ላይ ፈተና እየሆነ ይገኛል።
የስርቆት ችግሩም ከመደበኛ ሥራቸው ይልቅ በአስቸኳይ የጥገና ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ እያስገደዳቸው ስለመሆኑም አመልክተዋል።
የስርቆት ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል በተቋሙና በሪጂኖች የተለያዩ ሥራዎች ቢከናወኑም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሆኑ ከተቋሙ አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ነው ኃላፊዎቹ ያነሱት።
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ተቋሙ ከከፍተኛ የመንግስት አካላት ጋር በመወያየት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የኃይል መቆራረጥ እንዲያጋጥም ከማድረግ ባለፈ ተቋሙን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገው እንደሚገኝም ተገልጿል።