የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ78 ዓመታት የስኬት ጉዞውን በማስመልከት በልዩ ዝግጅት ወደ ካይሮ በረራ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ78 ዓመታት የስኬት ጉዞውን በማስመልከት በልዩ ዝግጅት ወደ ካይሮ በረራ አደረገ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ78 ዓመታት የስኬት ጉዞውን በማስመልከት በታሪኩ የመጀመሪያ በረራ ወዳደረገበት ካይሮ ዛሬ ምሽት በልዩ ዝግጅት በረራውን አድርጓል።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1946 መጋቢት 29 በአሥመራ በኩል በማድረግ ወደ ግብጽ ካይሮ በ/5C-47/ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ማድረጉ ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት በተደረገው ልዩ ጉዞ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻና ሌሎችም የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ወደ ካይሮ ለሚበሩ ደንበኞች የመስተንግዶ አገልግሎት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አየር መንገዱ በትጋት በመስራቱ ለስኬት በቅቷል።
በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ የብራንድ አምባሳደር ከመሆን አልፎ የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአየር መንገዱ የስኬት ምንጭ ደንበኞቹ መሆናቸውን በመግለጽ በዕለቱ በአየር መንገዱ እየተገለገሉ ላሉ መንገደኞች ስጦታ በመስጠት አመስግነዋል።
አየር መንገዱ የዛሬ 78 ዓመት የመጀመሪያውን በረራ የጀመረባት ካይሮ ዛሬ ላይ በየቀኑ የማያቋርጥ በረራ ከሚያደርግባቸው የአፍሪካ ከተሞች አንዷ መሆኗንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑትን የጀት ምርቶች በማስገባት ቀዳሚ ሲሆን፤ የመጀመሪያዎቹን የ/B767/፣ /B777-200LR/፣ /B787/ ድሪም ላይነር እና የ/787-9/ አውሮፕላኖችን በፍጥነት ወደ ገበያው በማስገባት የላቀ ውጤት ሲያስመዘግብ ቆይቷል።
ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው ጉዞው አየር መንገዱ ዛሬ ባሉት 147 አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ሲሆን፣ በካርጎ አገልግሎቱም በ16 አውሮፕላኖች ወደ 67 ዓለም አቀፍ ከተሞች ይበርራል።
በተጨማሪም በቅርቡ ከ100 በላይ ዘመናዊና ግዙፍ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት አድርጎ አውሮፕላኖቹ በትዕዛዝ ላይ ይገኛሉ።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።