የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ሠራተኞች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ሠራተኞች አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሠራተኞች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ዓላማ ጎን ለጎን ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሙያዊ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሠራተኞችም የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎቹ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመልዕክታቸውም አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ የፀጥታ ችግሮች ውስብስብና ተለዋዋጭ ባህሪያት ያላቸው በመሆናቸው ይህን ለመከላከል ሙያዊ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰልጣኞቹ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ በከተማው የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችን ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከማዕከል እስከ ወረዳ ያለው የሰው ኃይል በዕውቀትና በአመለካከት ታንጾ፤ ግብዓት ተሟልቶለት ዘመናዊ የፀጥታ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ ኃላፊዋ ገልጸዋል።
አያይዘውም ተመራቂዎቹ የተሰጣቸውን ስልጠና እንደ ተጨማሪ አቅም በመጠቀም አዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነባት፤ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት እና ለኑሮ ተመራጭ ከተማ ሆና የማየት ራዕይን ከዳር ለማድረስ የሚጠበቅባቸውን ድርብ ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ስልጠናው በወጣለት መርሃ ግብር መሰረት እንዲጠናቀቅ ትልቅ ሚና ለነበራቸው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኃላፊዎችና ድጋፍ ሰጪ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በስልጠናው 154 ወንድ እና 95 ሴት አመራርና ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።