ሀገራዊ ለውጡ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት አጎናጽፏል - አቶ አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት አጎናጽፏል - አቶ አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ፤ መጋቢት 29/2016(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የመወሰን መብት ማጎናጸፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንደገለጹት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በነበሩ 30 ዓመታት የክልሉ ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ የተለያዩ የእኩልነትና የመብት ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ለውጡን ተከትሎ የክልሉ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ የመወሰን መብት ማግኘቱንና በሚገባ ራሱን በራሱ ማስተዳደር መጀመሩን ገልጸዋል።
ከምንም በላይ በሀገራዊ ጉዳዮች ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል መወሰን መቻሉ ደግሞ የክልሉ ህዝብ በሀገራዊ ለውጡ ያገኘው ትሩፋት መሆኑን አስረድተዋል።
በሀገር ደረጃ በልማት እየተመዘገቡ ላሉ ስኬቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ድርሻ የላቀ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና መሠል ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከፍጻሜ እየደረሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለማደናቀፍ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውሰው በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሚሰሩ ጠንካራ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎች የጥፋት አካላት ሴራ እንደማይሳካ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በሀገራዊ ለውጡ ለተመዘገቡ ውጤቶች እውቅና ለመስጠት ላሳየው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፣ በለውጡ መንግስት የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በየዘርፉ የሚደረገው ርብርብ እንደሚጠናከር አስገንዝበዋል።
የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም አብዱረሂም በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በቱሪዝምና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የአሶሳ ከተማ ህዝብ የድጋፍ ሰልፍ ማድረጉ ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ ለውጡን ለመራው መንግስት እውቅና ከመስጠት ባለፈ አጋርነቱን በተግባር ያሳያል ብለዋል።
በተለያዩ መስኮች ውጤታማነትና ተጠቃሚነትን ማስቀጠል የሚቻለው ሠላማችን ዘላቂ ሲሆን ነው ያሉት ከንቲባው፣ የከተማው ነዋሪዎች ወንድማማችነትና እርስ በርስ መቻቻልን በማጠናከር ሠላማቸውን እንዲያስቀጥሉም አሳስበዋል።
ከድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አሙና አብዱልዋሂድ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአካባቢያቸው በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በተለይ በራሳችን ጉዳይ ራሳችን መወሰን መቻላችን የተጠቃሚነታችን ዋነኛ ማሳያ ነው ያሉት ነዋሪዋ፣ በክልሉ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ህብረተሰቡ ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መምጣቱን ተናግረዋል።
አቶ እንድሪስ አልመሃዲ የተባሉ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው የክልሉ ወጣቶች በነጻነት ተደራጅተው በመስራት ራሳቸውን ከመለወጥ በሻገር ለክልሉ ብሎም ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገራዊ የለውጥ ጉዞን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ ከተሞች እድገት በማሳየታቸው ህዝብን በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች በሀገራዊ ለውጡ የመጡ ውጤቶችን የሚደግፉ የተለያዩ መልዕክቶችን አሰምተዋል።