ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የምናደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን-የድሬዳዋ ነዋሪዎች 

ድሬዳዋ ፤ መጋቢት 29/2016 (ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ  ገለጹ።

በአስተዳደሩ በተያዘው ዓመት ለግድቡ ግንባታ የሚውል 12 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ነዋሪዎች እንደተናገሩት ለአገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ጉልህ አስተዋጽኦ ለሚኖረው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ያጠናክራሉ።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ደረጀ ጎሽሜ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ሲጀምር ለወጣቱ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ በመግዛት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የመቀስቀስ ሥራ እንደሚሰራ ተናግሯል።

በጥበቃ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ዋሲሁን ታደሰ ከወር ደመወዛቸው ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን እያሳረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለልጆቻቸውና ለትውልዱ ትልቅ ተስፋ የሆነው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።


 

አቶ ዘላለም ሁንዴ የተባሉት ነዋሪ ግድቡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጥና ''ይቻላል''ን ያስተማረን የአሁኑ ትውልድ ድንቅ የልማት ውጤት ነው ብለዋል።

ለግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ቦንድ በመግዛት ያደረጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አሰፋ በአስተዳደሩ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉን ገልጸዋል። 

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የአስተዳደሩ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ ተቋማትና ሠራተኞች የ2 ሚሊዮን ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የግድቡ መሠረት የተጣለበት 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚዘጋጁ ሁነቶች 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሕዳሴው ግድብ ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሻገር ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሀብታሙ፤ ድሬዳዋን የምስራቁ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግም እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ባለፉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በመቀጠል የግድቡን ግንባታ ከፍጻሜ እንዲያደርሱት ጠይቀዋል።

ከድሬዳዋ አስተዳደር ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና በስጦታ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ከ95 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 5ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።

ግድቡ በአራት ዙሮች 42 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ይዟል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም