ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2016(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ 13 አመታትን አስቆጥሯል፡፡ 

የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት ባለፉት አራት ተከታታይ አመታት የግድቡን ውሃ ሙሌት በስኬት በማከናወን በአሁኑ ወቅት ግድቡ ከ 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ ይዟል፡፡ 

የግድቡ ግንባታ ባለፉት አስራ ሶስት አመታት በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ አሁን ላይ 95 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሁለት ተርባይኖች ብቻ 750 ሜጋ ዋት በማመንጨት ኢትዮጵያውያንን የልማቱ ተቋዳሽ ማድረግ ተችሏል፡

ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ ድጋፋቸውን ሲያደርጉ የቆዩ ኢትዮጵያውያን አሁንም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ዘሪሁን ፈቃዱ "ህዳሴ ግድባችን አይናችንና የልብ ትርታችን ነው" ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የአስር ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን በመግለጽ፤ በቀጣይም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የአምስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የገለጹት ሀደ ስንቄ አረጋሽ ገዳ "በቀጣይም በላባችን እዚህ ያደረስነው ግድብ እስኪጠናቀቅ ድጋፌን አላቋርጥም" ብለዋል፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን "የዚህ ትውልድ ምልክት" የሆነው ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህጻን አዋቂ ሳይል ሁሉም የተረባረበበት መሆኑን ያወሱት አቶ አሸናፊ ሐይለማርያም በቀጣይም ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደማይቋረጡ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን የተሰበሰበው ድጋፍ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም