የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ በድሬዳዋ ስታዲየም ይከናወናሉ።
በመርሃ ግብሩም ሀዲያ ሆሳዕና ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት እንዲሁም ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በዚህም በ27 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ አቻ ተለያይቷል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
አዳማ ከተማ በ30 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌላኛው የ20ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድን ጋር ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ሲሆን በሁለቱ ሲሸነፍ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በዚህም ክለቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች 23 ነጥቦችን በመሰብሰብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 12ኛ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ሲሆን አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በአራቱ ነጥብ መጋራት ችሏል።
መድን በ15 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ20ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች መቻልና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ምንም ግብ አቻ ሲለያዩ ባህር ዳር ከተማ ሻሸመኔ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።