ቀጥታ፡

በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያላው የኮሪደር ልማት የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽልና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር ነው - የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያላው የኮሪደር ልማት የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽልና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በመዲናዋ በርካታ ዘመናትን የተሻገሩ መሰረተ ልማቶችንና ቤቶችን ለማዘመን፣ ለማደስና የነዋሪዎችን ፍታሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ይገኛል። 

የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ በማድረግ የአፍሪካ መዲናነቷንና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን የሚመጥን ቁመና ለማላበስ ያለመ ነው ተብሏል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከለወጡ ማግስት ጀምሮ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችንና በመከናወን ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል አቶ ብሩክ አለማየሁ እንዳሉት፣  እንደ አገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። 


 

በመዲናዋ የተገነቡ የአድዋ ሙዚየም፣ የአንድነትና የእንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ መስቀል አደባባይና መሰል የልማት ፕሮጀክቶች የለውጡ መንግሥት የልማት ትሩፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በመሆኑም የመልሶ ማልማት ሥራው የዜጎች ኑሮ የሚያሻሽልና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ልንተባበር ይገባል ነው ያሉት። 

ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ጣሰው ገመቹ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ሰፊውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


 

የኮሪደር ልማቱም በችግር ውስጥ የነበሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችን ሕይወት የታደገ እና የአኗኗር ዘያቸውን የቀየረ በመሆኑ ልንደግፈው ይገባል ብለዋል።

የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ የዜጎችን ህይወት ለመቀየርና የሥራ እድልን ለማስፋት ታልሞ በተከናወኑ ሰው ተኮር ተግባራት ትርጉም ያለው ለውጥ መመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ አቶ ወንድማገኝ ገረመው እና ዘርይሁን ፈቃዱ ናቸው፡፡


 

ህዝቡ መንግሥት የኢትዮጵያ መልክ የሆነችውን አዲስ አበባ ከተማን ለመለወጥ እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም