ቀጥታ፡

ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን---የድጋፍ ሰልፉ ታዳሚዎች

ሚዛን/ሆሳዕና/ሶዶ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦የለውጡ መንግስት ፈተናዎችን እያለፈ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ የሚዛን፣ የሆሳዕናና የወላይታ ሶዶ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች ገለፁ።

አገራዊ ለውጡን የሚደገፉ ሕዝባዊ ሰልፎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ተካሄደዋል።

በሚዛን አማን፣ በሆሳዕናና በወላይታ ሶዶ ከተሞች ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉን የታደሙ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ ስኬቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው።

በለውጡ መንግስት እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ተግባራት በተጨባጭ ህዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የለውጡ መንግስት ፈተናዎችን እያለፈ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንቆማለን ብለዋል።

የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ሀብተማርያም ካዝንቴት፤ በአካባቢያቸው ከለውጡ ወዲህ በሁሉም ዘርፍ የሚያስደንቅ ልማት እያዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለሁሉ ነገር ሰላም መሰረት መሆኑን አንስተው አብሮነትና ወንድማማችነትን በማስቀደም ለሰላም መጠበቅ የድርሻችንን መወጣት ይገባናል ብለዋል።

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው አቶ ተመስገን አበበ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ የመንገድና መሰል ለረጅም ዘመናት ይነሱ የነበሩ  ጥያቄዎች በአፋጣኝ ከፍጻሜ ሲደርሱ እየተመለከቱ መሆናቸውን ገልፀው ተግባሩ እንዲጠናከርም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በለውጡ መንግስት ሰላምን፣ አንድነትንና መደጋገፍን ለማጎልበት የተደረጉ ጥረቶች የሚደነቁ ናቸው ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ውድነሽ ገዛኸኝ ናቸው።

በተለይም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ውይይትን በማስቀደም አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በማደራጀት እየተከናወነ ያለውን ተግባር በአድናቆት እንደሚያዩት ገልፀዋል።

የመጣውን የለውጥ ዕድል በልማት አስደግፈን ለተሻለ እድገት እንተጋለን ያሉት የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው አቶ ንጉሴ ሳፕምቴት የትኛውንም ፈተና መመከት የሚቻለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር መሆኑን በአፅንኦት አስረድተዋል።


 

ሌላኛዋ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ በላይነሽ ሽፈራው መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይ ለተሻለ ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት አለብን ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ ህዝብን ወርዶ የሚያዳምጥና ችግሮችን በተገቢው መንገድ ለይቶ የሚመልስ ስርዓት በመዘርጋቱ ተጠቃሚ ሆነናል ያሉት ደግሞ በሃዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ነዋሪው አቶ ተሻለ ኤሪሶ ናቸው።

በተለይም አስተዳደሩ ከህዝብ ጋር በቅርበት ለመስራት የሚያደርገው ጥረት ከሁሉ በላይ የሚያስደስት መሆኑና ዕውቅና መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም በበኩላቸው ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የለውጥ ስራዎች ከተማዋ ተጠቃሚ መሆኗን አስታውቀዋል።


 

በከተማዋ አየር ማረፊያን ጨምሮ የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የደንቢ ሎጅና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በመንገድና በውሃ እንዲሁም ሲጓተቱ የነበሩ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ አዳዲሶችን የማጠናቀቅ፣ ግብርናን የማዘመን፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከርና መሰል ትሩፋቶች መታየታቸውን ያነሱት ደግሞ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ ናቸው።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው፤ የድጋፍ ሰልፉ ዓላማ በለውጡ መንግስት መሪነት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠል መሆኑን ገልፀዋል።

በለውጡ ዓመታት ለዘመናት ጥያቄ ሆነው የዘለቁ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ከፍተኛ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ ላለፉት ስድስት ዓመታት በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች ተጨባጭ ድሎች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት የተለያየ የፖለቲካ እሳቤን የማስተናገድ፣ የአደረጃጀትና የወሰን ጥያቄዎች የመመለስ ጉዳዮችን ለአብነት አንስተዋል።

በየከተሞቹ በተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች ላይ የተገኙ ነዋሪዎች በለውጡ መንግስት የተመዘገቡና እየተመዘገቡ የሚገኙ የልማት ድሎችን በመጠበቅ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም