ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ወንጀል ፈፃሚዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ወንጀል ፈፃሚዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ከዘረፉት ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ወንጀሉን የፈፀሙ አካላትን ለመቆጣጠር የምርመራና የክትትል ቡድኑ ሌት ከቀን በመስራት ውጤት ማምጣት መቻሉን ፖሊስ ገልጿል፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አሽከርካዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተ-ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ ወጣት ሶፎኒያስ አስራት ተገድሎ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
የወጣቱ መገደል ሪፖርት የደረሰው አዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ እና የክትትል ቡድኖችን በማዋቀር የገዳዮቹን ማንነት ለማወቅ ወንጀለኞቹን ህግ ፊት ለማቅረብ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሷል፡፡
ሟች ወጣት ሶፎኒያስ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ናሆም ሆቴል አካባቢ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው የማይታወቁ ሦስት ግለሰቦችን በግል በተደረገ ስምምነተ ያለአፕልኬሽን ምዝገባ በኮድ 2 ቪትዝ አሳፍሮ ወደ ቦሌ ሚካኤል ለማድርስ መሄዱን ጉዳዩን ለመመርመር የተቋቋመው የምርመራና የክትትል ቡድን አባላት ባሰባሰቡት ማስረጃ ማረጋገጣቸውን ፖለስ አክሏል፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀል ለመፈፀም አቅደው እና ተደራጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ሹፌሩን በመቅረብ ካሳፈራቸው በኋላ አንገቱን በገመድ አንቀው በመግደል አስክሬኑን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በመጣል አይነቷ ቪትዝ የሴሌዳ ቁጥር ኮድ 2A 93488 ተሽከርካሪ ጨምሮ ሁለት ሞባይል ስልኮችን ዘርፈው መሰወራቸው ተጠቁሟል፡፡
ፖሊስ ወንጀሉ ከተፈፀመበት ጊዜ አንስቶ ቀን ከሌት ባደረገው ብርቱ ክትትል ልዩ ልዩ ፖሊሳዊ ቴክኒኮችን በመጠቀም ወንጀል ፈፃሚዎቹ የሰረቁትን ተሽከርካሪ፣ ሦስቱን ዋና ወንጀል ፈፃሚዎች እና የሰረቁትን መኪና እንዲሁም ሶስት አባሪዎቻቸውን መያዙን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ከወንጀል ፈፃሚዎቹ እጅ ላይ ባለቤታቸው የማን እንደሆኑ የማይታወቁ 7 የስልክ ሲም ካርዶችን ይዞ ምርመራው መቀጠሉን ጨምሮ ገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ወንጀሉ በስውር የተፈፀመና ማንነታቸው የማይታወቁ ቢሆንም በተደረገ ብርቱ ክትትል ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በመለየት ሦስት ዋና ወንጀል ፈፃሚዎችን እና ሦስት ግብራበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ጠቅሷል፡፡
ለዚህ ስራ ስኬታማነት ቀና ትብብር ላደረጉ አካላት አዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቦ፤ የምርመራ ሥራው እንዳበቃ የፍርድ ሂደት ውጤቱን በቀጣይ ለህዝብ እንደሚገለፅ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ህጉን ጠብቀው አገልግሎት ሲሰጡ በአፕልኬሽኑ ተመዝግበው እንዲሆን ፖሊስ አሳስቧል።