በአማራ ክልል የሴት አመራር አባላትን ቁጥር ለማሳደግ ለአቅም ግንባታ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷል - ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሴት አመራር አባላትን ቁጥር ለማሳደግ ለአቅም ግንባታ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷል - ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ

ባህርዳር ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሴት አመራር አባላትን ቁጥር ለማሳደግ ለአቅም ግንባታ ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ገለፁ።
የክልሉ የሴት አመራሮች ፎረም የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለፁት፤ በየደረጃው ባለው የመንግስት መዋቅር፣ በልማት ድርጅቶችና በሌሎች ተቋማት የሴት አመራሮችን ቁጥር ማሳደግ ይገባል።
ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ የወንድና የሴት አመራር አባላትን ቁጥር ለማመጣጠን ፎረሙን ጨምሮ ሌሎች የሴት አደረጃጀቶችን የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።
ሴቶችን በአደረጃጀቶች በማሳተፍ፣ በስልጠናና በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በማጎልበት የአመራር ብቃታቸውን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ነው ያሉት።
''ሴቶችን በተግባር ተኮር ስራዎች በማሳተፍ ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውን ለማሳደግ ሁላችንም በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል'' ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ በበኩላቸው፤ ፎረሙ በየደረጃው ያለውን የሴት አደረጃጀቶች ማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት።
በክልሉ የሴቶች የአመራር ሰጪነት ሚና የበለጠ እንዲያድግ በሁሉም ረገድ ሴቶችን የማብቃት ስራዎች ትኩረት ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
''ፎረሙ ሲመሰረት የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶች ወደ አመራርነት የሚመጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ናቸው።
ከክልል እስከ ወረዳ ያለው የሴት አመራር አባላት ቁጥር በአማካይ ከ25 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቁመው፤ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ ብለዋል።
በክልሉ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ግርማ መለሰ በበኩላቸው፤ ብቃታቸው ከፍ ያለ የሴት አመራር አባላትን ለማፍራት በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ ዛሬ በተካሄደው የፎረሙ የምክክር መድረክም ከክልሉ ቢሮዎች፣ ከልማት ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አመራር አባላትና ከሌሎች ተቋማት የተውጣጡ የሴት አመራሮች ተሳትፈዋል።