ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማሳካት በትጋት ልንሰራ ይገባል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦  በጋምቤላ ክልል ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማሳካት በትጋት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

‘‘ለሀገራችን ብልጽግና በህብረት እንቆማለን’’ በሚል መሪ ሃሳብ  ለውጡንና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ የድጋፍ ሰልፉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙትን የልማት ስኬቶችና ቱሩፋቶች አጠናክሮ በማስቀጠልና የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማስፋት በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየርና ያሉትን ጸጋዎች በማልማት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ተግባር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ፣ በግብርና ልማት፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ድሎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰው ግድቡ ግንባታ ፍፃሜ እንዲደርስ የክልሉ ህዝብ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የቆየውን ተሳትፎና ድጋፍ ሊያጠናከር ይገባል ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጋትሉዋክ ጋች በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።


 

አብሮነትና አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከፍፃሜ ላይ በማድረስ የብልጽግና ጉዞውን እውን ለማድረግ በትብብር ልንሰራ ይገባል ብለዋል ከንቲባው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም