የፓርላማ ዲፕሎማሲን የሚያጠናክሩና የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ሥራዎች ተሰርተዋል - ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የፓርላማ ዲፕሎማሲን የሚያጠናክሩና የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ሥራዎች ተሰርተዋል - ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፓርላማ ዲፕሎማሲን የሚያጠናክሩና የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ ሥራዎች መሠራታቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ምክር ቤቱ በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ የፓርላማ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ አገራት የፓርላማ አባላትን ተቀብሎ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየቱን ነው ያነሱት።
ከፓርላማ አባላቱ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የሕዝብ ለሕዝብና የፓርላማ ለፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማጠናከር መቻሉንም ተናግረዋል።
ከፓርላማ አባላትና ከአገራት አምባሳደሮች ጋር የተካሄዱት ውይይቶች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ለማስረዳት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ይህም ከአገራቱ ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ዕድል መፍጠሩንም እንዲሁ።
ከተለያዩ አገራት የፓርላማ አባላት ጋር በተደረገ ውይይት የአገር ገጽታ ለመገንባት ጉልህ ሚና እንደነበረውም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስረድተዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ከአንዳንድ አገራት ጋር የነበረው አለመግባባት በፓርላማ ለፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነቱ እንዲሻሻል መደረጉን ገልፀዋል።
ከአገራት የፓርላማ አባላት ጋር በሚደረግ ውይይት ኢትዮጵያ እያከናወነች ስላለችው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማብራሪያ መስጠት መቻሉን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መገንባቷ ከአገሪቷ አልፎ ለሌሎች አገራት ያለውን ሚና በተመለከተ ገለፃ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ሌሎች የምታከናውናቸው ተግባራትን ማስረዳት ተችሏል ነው ያሉት።
በቀጣይም ቋሚ ኮሚቴውና በምክር ቤቱ የተቋቋመው የወዳጅነት ቡድን አባላት የፓርላማ ዲፕሎማሲ ሥራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት ይሰራሉ ብለዋል።