ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ78 ዓመታት የስኬት ጉዞውን በማስመልከት በልዩ ዝግጅት በረራ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ78  ዓመታት የስኬት ጉዞውን በማስመልከት በታሪኩ የመጀመሪያ በረራ ወዳደረገበት ካይሮ  በልዩ ዝግጅት በረራ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1946 መጋቢት 29 በአሥመራ በኩል በማድረግ ወደ ግብጽ ካይሮ በ/5C-47/ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን አደረገ።

የኢቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በተቀላቀለበት 78 ዓመታት ጉዞው በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ በስኬታማነት በአፍሪካ ግዙፍ የአየር ትራንስፖርት ኩባንያ መሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያዴቻ፤ አየር መንገዱ በኢቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሁንም በፍጥነት እያደገ ያለ ግዙፍ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።

በአህጉሪቷ የመጀመሪያ የሆኑትን የጀት ምርቶች በማስገባት ቀዳሚ ሲሆን፤ የመጀመሪያዎቹን የ/B767/፣ /B777-200LR/፣ /B787/ ድሪም ላይነር እና የ/787-9/ አውሮፕላኖችን በፍጥነት ወደ ገበያው ያስገባ ስኬታማ አየር መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆኑትን የአልትራ ሞደርን ኤር-ባስ /A350-900/ አውሮፕላኖችን በወቅቱ በብቸኝነት በመግዛት ወደ ሥራ ያስገባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ የኩራት መገለጫና የብራንድ አምባሳደር ከመሆኑም በላይ የአፍሪካውያን የስኬት ማሳያና የኩራት ምንጭ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በተለይም አፍሪካን ከአውሮፓና ከተቀሩት የዓለም አገራት ጋር በማስተሳሰር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በየጊዜው እያዘመነና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር በመከተል በፍጥነት እያደገ ይገኛል ነው ያሉት።

ለአየር መንገዱ የስኬት ጉዞም የሠራተኞች ብርቱ ትጋት፣ የጠንካራ ስትራቴጂክ አመራር ብቃት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ አሠራሮችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ከሰባት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን ስኬት በማስመልከትም የመጀመሪያ በረራውን ወዳደረገበት ካይሮ ነገ እሁድ ምሽት በልዩ ዝግጅት ለመብረር መዘጋጀቱን አቶ ለማ ገልፀዋል።

በእለቱም የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ለደንበኞች ልዩ የመስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 የስታር አሊያንስ አባል ለመሆን የበቃ ሲሆን፤ ይህም በዓለም አቀፉ ግዙፍ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ውስጥ ያለውን ሚና የላቀ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

አየር መንገዱ በራዕይ 2025 ለ15 ዓመታት ባስቀመጠው ግብ መሠረት 25 በመቶ እድገቱን በዕቅዱ ማሳካት መቻሉን ገልጸው፤ ለራዕይ 2035 ፍኖተ-ካርታም ከወዲሁ ስኬቶችን እየተጎናፀፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በ147 አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፤ በካርጎ አገልግሎቱም በ16 አውሮፕላኖች 67 ዓለም አቀፍ ከተሞች ይበራል።

በአፍሪካ  ከ63 በላይ ከተሞች በመብረር አህጉራዊ ትስስሩን እያፋጠነ ስለመሆኑም አንስተዋል።

አሁን ላይ ከ100 በላይ ዘመናዊና ግዙፍ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት አድርጎ አውሮፕላኖቹ በትዕዛዝ ላይ ናቸው ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም