ለውጡ የህዝብን ጥቅም ያረጋገጠ ነው - የሰልፉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለውጡ የህዝብን ጥቅም ያረጋገጠ ነው - የሰልፉ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ ለውጡ የህዝብን ጥቅም ያረጋገጠ ነው ሲሉ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ የለውጡን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ "ለሀገራችን ብልጽግና በህብረት እንቆማለን" በሚል መሪ ሀሳብ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ስድስት የለውጥ አመታት የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል።
አቶ ብርሃኑ ኤርገዳ እንዳሉት በለውጡ አመታት የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተሰርተዋል።
ህብረተሰቡን ተፋፍጎና ተነባብሮ ከሚኖርበት አስከፊ የኑሮ ሁኔታ እንዲወጣ በተሻለና ዘመኑን በዋጀ መኖሪያ ቤት እንዲኖር እየተደረገ ያለው የመልሶ ማልማት ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ላቀው ሄራኖ በበኩሉ በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፉት ፣ በቤቶች ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራትና መሰል ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ ከለውጡ ወዲህ ለተማሪዎች እየተሰጠ ያለው ምገባ መንግስት የተሻለ ትውልድ ለማፍራት ያሳየውን ቁርጠኝነት የሚያሳይና የሚያስመስግ ነው ብለዋል።
በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች የታደሙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየሰጡት ያለውን አመራር የሚደግፉና ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገኙትን ለውጦች የሚገልጹ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
ሰልፈኞቹ ይዘዋቸው ከወጡ መልእክቶች መካከል አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ትሆናለች፣ ሰላማችን በእያንዳንዳችን ቤት ናት፣ በለውጡ መሪ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው እና አገራችንን ወደ ከፍታ ለማሻገር ከለውጡ አመራር ጋር በጽናት እንቆማለን የሚሉ ይገኝበታል።