ቀጥታ፡

በወላይታ ሶዶና አርባ ምንጭ ከተሞች በለውጡ መንግስት የተገኙ ስኬቶችን የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

ሶዶ/አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶና አርባ ምንጭ ከተሞች ባለፉት ዓመታት በለውጥ መንግስት የተገኙ ስኬቶችን የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ  እየተካሄደ ነው።

የድጋፍ ሰልፉ "ለሀገራችን ብልፅግና በህብረት እንቆማለን" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።


 

በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በዞኑ ከሚገኙ የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ናቸው።

የድጋፍ ሰልፉ ዓላማ ባለፉት ስድስት ዓመታት በለውጥ መንግስት የተመዘገበውን ሁለንተናዊ የልማት ውጤቶች በህዝቡ ተሳትፎ ማፅናትን ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች "ሰላማችን የብልጽግናችን መሠረት ነውና ለሀገራችን ሰላም ተያይዘን እንሰራለን"፣ "ህብረ ብሔራዊነታችንን በማጠናከር ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እንገነባለን" የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን እያሰሙ ነው።

በተመሳሳይ በክልሉ በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ የለውጡ መንግስት እያስመዘገበ ያለውን ውጤት የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

መንግስት የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ውጤት ማስመዝገቡን የሚያመለክቱ መፈክሮችንም እያሰሙ ነው።

ሰልፈኞቹ ከ"ለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ ሆነናል"፣ "ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን"፣ "ህዳሴያችን እናረጋግጣለን"፣ ''የብልጽግና ጉዞ አይደናቀፍም" የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ላይ ናቸው።

በአርባምንጭ ሁለ ገብ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ በጋሞ ዞን ከሚገኙ የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም