ቀጥታ፡

ለውጡ ለአዲስ አበባ በርካታ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመጣ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2016(ኢዜአ)፦ አገራዊ ለውጡ ለአዲስ አበባ በርካታ ገጸ በረከቶችን ይዞ የመጣ መሆኑን ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ የለውጡን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ "ለሀገራችን ብልጽግና በህብረት እንቆማለን" በሚል መሪ ሀሳብ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ ለውጡን ተከትሎ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ለከተማዋና ለነዋሪዎቿ በርካታ ትሩፋት ያመጡ ናቸው።

የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ ፓርኮች ግንባታ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ማስፋፊያ፣ ሰው ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ሌሎች የልማት ስራዎች የነዋሪውን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

በተለይም የኑሮ ውድነትን ለመፍታት ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ በማድረገ ዋጋን የማረጋጋት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው በዚህም በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት።


 

በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር በርካታ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው በየጊዜው የሚደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል።

አገራዊ ለውጡ ለአዲስ አበባ በርካታ ገጸ በረከቶች ይዞ መጥቷል ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህንን ለውጥ የማስቀጠል ሃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመስቀል አባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች የታደሙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እየሰጡት ያለውን አመራር የሚደግፉና ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገኙትን ለውጦች የሚገልጹ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ሰልፈኞቹ ይዘዋቸው ከወጡ መልእክቶች መካከል አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ ትሆናለች፣ ሰላማችን በእያንዳንዳችን ቤት ናት፣ በለውጡ መሪ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው እና አገራችንን ወደ ከፍታ ለማሻገር ከለውጡ አመራር ጋር በጽናት እንቆማለን የሚሉ ይገኝበታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም