ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት በማጠናከር አካታች ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል - ማሞ ምኅረቱ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት በማጠናከር አካታች ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል - ማሞ ምኅረቱ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓትን በማስፋትና በማጠናከር አካታች ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ገለጹ።
የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፤ ዓለም የእጅ በእጅ የገንዘብ ክፍያን በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት እየቀየረች የምትገኝበት ወሳኝ ዘመን ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱም ዜጎች በእጅ ስልክ፣ በላፕቶፕና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ፈጣንና ታማኝ የገንዘብ ክፍያ እንዲፈጽሙ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በዘርፉ የወሰደችው የፖሊሲ እርምጃ አካታችና ቀልጣፋ የኢኮኖሚ እድገት እንዲፈጠር በማድረግ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ፋይናንስ ክፍያ ሥርዓት ለአካታች ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት የማይተካ ሚና ስላለው ለዘርፉ እድገት በቴክኖሎጂ ልማት ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የዲጂታል ፋይናንስ ክፍያ ሥርዓት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሞባይል ባንኪንግ፣ የኤቲ ኤምና መሰል የዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንንም ተከትሎ አብዛኞቹ ክፍያዎች በዲጂታል ሥርዓት እየተፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።
በብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሒሳብ ማወራረጃ ሥርዓት ዳይሬክተር ሰለሞን ዳምጠው፤ በኢትዮጵያ ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መጠቀም የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የባንክ ሒሳብ ያለው ማንኛውም ሰው በባንኮች አማካኝነት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን መጠቀም የሚያስችለውን መሰረተ ልማት እንደተሟላለት ገልጸዋል።
ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያስገኘውን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት መጠቀም ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱንም አስረድተዋል።
የኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ይላበስ አዲስ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ተናባቢ የፋይናንስ ምኅዳር መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በዚህም የገንዘብ ተቋማት ተናባቢ የዲጂታል ክፍያ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸው በማድረግ ዜጎች ገንዘብን በቀላሉ የሚያንቀሳቅሱበት ሥርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
ማኅበሩም የብሔራዊ ባንክ የዲጂታልና የአካታች ፋይናንስ ስትራቴጂክ ተግባራትን በመውሰድ ለፈጣን የገንዘብ አገልግሎት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ ዜጎች በግብይት ሂደት ላይ በአንድ ማዕከል ተናባቢ የዲጂታል ገንዘብ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡበትና የሚገኙበት "ኪው አር ኮድ" ይፋ ሆኗል።
መድረኩም በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ስትራቴጂክ ተደራሽነት፣ ደኅንነትና ቅልጥፍና በዘርፉ የመጡ ለውጦች ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።