የአየር ንብረት ለውጥና መዘዙ

1435

በዓለማችን ላይ እየተስተዋለ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የተወሳሰበ ችግር እያስከተለ ከመሆኑ በተጨማሪ  በስነምህዳር ላይ እያደረሰ ያለው አደጋ ሊቀለበስ ወደ ማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን ሞደርን ዲፕሎማሲ ድረገጽ አስነበበ። 

ድረ ገጹ በዓለማችን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ድርቅ፣ ጎርፍ እና ተዛማጅ በሆኑ ክስተቶች ምክንያት ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደሚገደዱ አስነብቧል።

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በይነመንግስታት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው አሁን ላይ ያለው የዓለማችን የሙቀት መጠን ወደ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴሊሺየስ እየተጠጋ በመምጣቱ በስነምህዳር፣ በከባቢ አየር እና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጿል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለዘላቂ ልማት እንቅፋት በመሆን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የሚፈጥራቸውን ችግሮች በማባባስ ለሰዎች መፈናቀልና የህይወት መጎሳቆል እያደረሰ ይገኛል።

እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 በማዕከላዊ አሜሪካ እና ደቡባዊ ሜክሲኮ የተከሰተው ሃሪኬን ኤታ የተባለው  የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ያስከተለው የሰብል ውድመትና የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የደረሰው አደጋ ከባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ውስጥ እጅግ የከፋ አደጋ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል። 

በዚህም በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተትና በሰብል ውድመት ምክንያት ከ1 መቶ 20 ሺህ በላይ ሰዎችን ከሞቀ መኖሪያቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽንን መረጃ ዋቢ አድርጎ አትቷል። 

የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆመው ድረ ገጹ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም አመልክቷል።

በአውሮፓውያኑ 2022 ወደ 32 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ በ2008 ከተከሰተው በ41 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዘገባው አመልክቷል። 

ይህም የዓለማችን የሙቀት መጠን እየጨመረ መምጣቱን እንጂ ምንም ዓይነት የመቀነስ አዝማሚያ ያላሳየ መሆኑን ያመለከተው ዘገባው በቺሊ፣ ካናዳ፣ ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሜክሲኮ፣ ኢክዋዶር፣ ሊቢያ እና በሌሎችም አገራት ሃሪኬን በተሰኘው የአየር ለውጥ፣ በሰደድ እሳት፣ በጎርፍ እና በድርቅ ምክንያት ለባለፉት በርካታ ወራት መፈናቀልን እንዳስከተለ ተገልጻል።

የአለም ባንክን የትንበያ መረጃ ዋቢ ያደረገው ድረ ገጹ በአውሮፓውያኑ 2050 ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ 216 ሚሊዮን ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ተመላክቷል። 

ድረገጹ ይሄ ክስተት የሚያስከትላቸው ችግሮች እንዳይቀጥሉ መቆጣጠር ካስፈለገ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮሩ ግንዛቤን የሚያሳድጉ ትምህርቶች፣ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ እውነተኛ ውይይቶች እና ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማሳሰብ መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሊተገብሩ ይገባል ሲል ምክሩን አስቀምጧል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም