ቀጥታ፡

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ችግሮችን በመሰረታዊነትና በዘላቂነት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ችግሮችን በመሰረታዊነትና በዘላቂነት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሚኒስትሮችና የተቋማት ሃላፊዎች በተገኙበት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ የሶስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩም ከ115 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር በርካታ ስብራቶችን ይዞ መቀጠሉ ተነስቷል።

ይህንን ለመቀየር በዘርፉ ላይ በፖሊሲ የተደገፈ አዲስ ዕይታና መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አስፈልጓል ተብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የኢትዮጵያ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር መሰረታዊ ችግሮች ስለነበሩበት ሀገራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦች በሚፈለገው ልክ እንዳይሳኩ አድርጓል ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ሳይፈቱ የቆዩ የልማትና የአገልግሎት ችግሮችን በመቅረፍ የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ከዳር ለማድረስም የተቋማት የማስፈጸም አቅም ደካማ መሆኑ ፈታኝ ሆኗል ነው ያሉት።

በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የወጡ እቅዶችንና ፖሊሲዎችን ለማሳካት የመንግስት የማስፈጸም አቅምን ማሻሻል ወሳኝ እንደሆነ አምኖ ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል።

ለዚህም በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ከተያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን ማሻሻል እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ ለማምጣት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሪቂቅ ፖሊሲ፣ አዋጅና ሌሎች የህግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ሲሆን በቅርቡ ፀድቀው በይፋ ወደ ትግበራ ይገባሉ ብለዋል።

ይህንን ሀገራዊ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ በእቅድ መመራት፣ የራሱ የሰው ሃይልና አደረጃጀት መድቦ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው የተቋማት አመራሮች ለተፈጻሚነቱ ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር፤) ከምዕተ ዓመት ላለፈ ጊዜ በኢትዮጵያ ሲተገበር የቆየው ሲቪል ሰርቪስ ሀገራችንን የማይመጥንና በርካታ ስብራቶች ያሉበት ነው ብለዋል።


 

የለውጡ መንግስት ይህንን ሀገራዊ ችግር በትኩረት በመቃኘት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም አስፈላጊ ረቂቅ ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ከጥር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ትግበራ በመጀመሪያው ዙር ስምንት ተቋማት ተለይተው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው እነዚህ ተቋማት ተልዕኮውን የማሳካትና ለቀሪዎቹ ተቋማት ተምሳሌት የመሆን ድርብ አደራ ተጥሎባቸዋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም