በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርኃ-ግብር ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል- ዶክተር ድረስ ሳህሉ

624

ባህር ዳር፤ መጋቢት 27 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በመጪው የክረምት ወቅት ለተከላ የሚውል  ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ድረስ ሳህል እንደገለጹት፤ በክልሉ ህዝቡን በስፋት በማሳተፍ በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። 

በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ርብርብ የክልሉ የደን ሃብት ትርጉም ባለው መንገድ መሻሻሉን ገልጸዋል።

በ2008 ዓ.ም የክልሉ የደን ሽፋን ከ10 በመቶ ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰው፤ በቅርቡ በተደረገ ጥናትና በብሔራዊ ቆጠራ (ናሽናል ሴንሰስ) መሰረት የደን ሽፋኑ 16 በመቶ ላይ እንደደረሰ መረጋገጡን አስታውቀዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ውጤት ለውጥ እየታየበት ያለ ተግባር በመሆኑም ህዝብን ባሳተፈ አግባብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገልጸዋል።

በቀጣዩ የክረምት ወቅትም ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ በማፍላት የተከላ ስራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የደን ሃብት ልማት ስራው ሁሉም አካል ሃላፊነት ወስዶ ሊሰራበት የሚገባ ተግባር በመሆኑም መጪው ክረምት ለችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መሳካት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

''በየዓመቱ የሚከናወነው የችግኝ ተከላ የደን ሽፈንን ከማሳደጉም በላይ ለሌሎች የግብርና ስራዎች ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው'' ያሉት ደግሞ በግብርና ቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ናቸው።


 

የችግኝ ተከላ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በመጪው ክረምት ለሚከናወነው የችግኝ ተከላም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለችግኝ ተከላውም ከ201 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን መታቀዱንና እስካሁን በተደረገ ጥረት  ከ135 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለተከላ ተለይቶ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ እስካሁን ባለው መረጃ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተፈልቶ እንደተሰናዳ በቆጠራ ተረጋግጧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም