ቀጥታ፡

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዳያስፖራ አባላት ገለጹ።    

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ 13 ዓመት ሆኖታል።

ግድቡ በኢትዮጵያዊያን ርብርብ ወደ መጠናቀቁ ምዕራፍ የተቃረበ ሲሆን አፈጻጸሙም ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።    

ለግድቡ ግንባታ በስኬት መካሄድ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ቦንድ በመግዛት፣ በኃሳብና በዲፕሎማሲ ያደረጉት ተሳትፎ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በአሜሪካን ሀገር ለበርካታ ዓመታት የኖሩት አቶ ኤርሚያስ መኮንን የግድቡ ግንባታ መሰረት ከተጣለ ጀምሮ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲያስተባብሩ ከነበሩ ሀገር ወዳድ ዜጎች መካከል ናቸው። 

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን (እርሳቸውን ጨምሮ) ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የዳያስፖራው ሚና ትልቅ ነው።  

የግድቡ ግንባታ ከፖለቲካ ጋር ሊያያዝ አይገባም፤ ወደ መጨረሻው የግንባታ ምዕራፍ የደረሰው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ የማድረግ የሞራል ግዴታ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።   

በዲፕሎማሲው መስክም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፤ ዲፕሎማሲው የበለጠ እንዲጠናከር የኛ የዳያስፖራ አባላት ተሳትፎ የበለጠ ሊጎላ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።    

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ከጫፍ ጫፍ ያሰባሰበ ወደ አንድነት ያመጣ፤ እንደ ዓይን ብሌናችን የምንጠብቀው ፕሮጀክታችን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው በአሜሪካ የዳያስፖራ አባል አቶ ተስፋዬ አየለ ናቸው።

በአባይ ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ድርድር የለም ያሉት አቶ ተስፋዬ ወደ ፊትም የግድቡ ግንባታ ማብቃቱ እስኪበስር ድረስ ድጋፋችን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቃለአብ ግርማ በበኩላቸው፤ ዳያስፖራው በግድቡ ዙሪያ በሁሉም መስክ ጠንካራ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።  


 

የዳያስፖራው ተሳትፎ የበለጠ እንዲጎለብት እኛም እንደ ዳያስፖራው አደረጃጀት ሚናችንን እንወጣለን ሲሉም አብራርተዋል።  

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማከናወን የመሰረት ድንጋይ የተጣለው መጋቢት 24/2003 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም