ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ በ850 ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ እስካሁን በ850 ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ፤ የምክክር ሂደቱ አሁን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የተሳታፊዎች ልየታና በአጀንዳ ግብዓት ማሰባሰቢያ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም በ850 ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ጠቅሰው 

የ100 ወረዳዎች ደግሞ በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀባቸው ክልሎች መሆናቸውንም ተናግረዋል። 

አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችም የተሳታፊዎች ልየታ ተጠናቋል ነው ያሉት።

በሱማሌ ክልል 25 ወረዳዎች እና በኦሮሚያ ክልል 70 ወረዳዎችም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው  በቀጣይ በአማራና ትግራይ ክልሎች ይከናወናል ብለዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩ ተሳታፊዎችም በቀጣይ በሚካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ ተቋማትን፣ ማህበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎችንም የወከሉት በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 በተያዘው እቅድ መሰረት በክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች ተወካዮች በተመሳሳይ ጊዜ ውይይቶችን የሚያደርጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ከቀናት በፊት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአማራ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ ለመጀመር ከክልሉ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልልም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ለሂደቱ አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ዙሪያ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑንም እንዲሁ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም