በሚያዚያና ግንቦት ወር የበልግ ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

569

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ በሚያዚያና ግንቦት ወር የበልግ ዝናብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።   

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሁለት የበልግ ወራት የነበረውን የአየር ጠባይ ግምገማና በሚቀጥሉት የበልግ ወራቶች የሚጠበቀው አየር ጠባይ አዝማሚያን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።  

በመግለጫውም፤ ባለፉት ሁለት የበልግ ወራት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት በደቡብ፣ ደቡብ ምሰራቅና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደነበር ተጠቅሷል።    

በሚያዚያና ግንቦት ወርም የበልግ ዝናብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር ትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል። 

ይህንንም ተከትሎ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል። 

የምዕራብ አጋማሽ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሰሜን ምስራቅ መካከለኛውና የምስራቅ የአገሪቱ አከባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም ትንበያው አሳይቷል። 

ኅብረተሰቡም ይህንን የአየር ጠባይ ትንበያ ከግምት በማስገባት የሚገኘውን ዝናብ ለግብርና እንቅስቃሴ ማዋል እንደሚገባና ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከባለሙያ ጋር በመመካከር ማካሄድ እንደሚገባ ተመላክቷል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም