በክልሉ ዘንድሮ ከ159 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል

579

ዲላ ፤ መጋቢት 27/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ከ159 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በህዝብ ተሳትፎ በለሙ አካባቢዎች ቡናን ጨምሮ ከ372 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉም ተመላክቷል።


 

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የተራቆቱና ተራራማ አካባቢዎችን ማዕከል በማድረግ ነው የተከናወነው። 

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በላቀ የህዝብ ተሳትፎ የተከናወነው የልማት ሥራ ለ30 ቀናት የተካሄደ ሲሆን በዚህም ከ159 ሺህ ሄክታር በላይ ለጉዳት የተጋለጠ መሬት እንዲለማ መደረጉን ሃላፊው ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው የጠረጴዛ እርከንን ጨምሮ የአፈር መከላትና መሸርሸርን የሚቀንሱ የተለያዩ ሥነ አካላዊ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው የገለጹት።


 

በልማት ሥራው ህብረተሰቡ በጉልበትና በተለያዩ መንገዶች ተሳትፎ ማድረጉንም አቶ ሀይለማርያም ገልፀዋል።

እንደሳቸው ገለጻ፣ በዘመቻው የአፈርና ውሃ ጥበቃ በተከናወነባቸው አካባቢዎች ቡናና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ከ372 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርም ህብረተሰቡን በነቂስ በማነቃነቅ በለሙ ተፋሰሶች ላይ የችግኝ ተከላ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን መድኔ በበኩላቸው በዞኑ በ361 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም 76ሺህ 973 ሄክታር መሬት ለማልማት መቻሉን የገለጹት አቶ መስፍን፣ የለማው መሬት በስነ ሕይወታዊ ሥራዎች በማጠናከር ለግብርና ልማት ሥራ ይውላል ብለዋል። 


 

በጌዴኦ ዞን ኮቸሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መክብብ መኮንን በበኩላቸው በልማቱ እርከንና የጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

በህዝብ ተሳትፎ የቡና ጉንደላ፣ የቡና መትከያ ጉድጓድ መቆፈርና የተለያዩ ተግባራት በልማቱ መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በወረዳው የብሎያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በግዱ ጀጎ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በየዓመቱ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ልማቱ እሳቸውን ጨምሮ የወረዳውን አርሶ አደሮች በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እያደረገ በመሆኑ በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ሥራ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። 

በተለይ በተራቆቱ አካባቢዎች ካከናወኗቸው የመኖ ሣር ተከላ፣ ክትርና፣ ጉድጓድ መቆፈር ሥራዎች በተጨማሪ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዘመቻው የእርከንና የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም እንሰት፣ ቡና እና ፍራፍሬ መትከል እንደጀመሩም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም