በሀገር አቀፍ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ 37 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ 37 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ 37 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የስፖርት ፖሊሲው መንግስት የዜጎችን አካላዊ እንቅስቃሴና ተሳትፎ ለማጎልበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲገነቡ፣ እንዲጠበቁና ተደራሽ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስቀምጣል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አዝመራው ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት ሕብረተሰቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ ጥያቄዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የማዘውተሪያ ስፍራዎች በሚፈለገው መጠን አለመዳረሱ ዜጎች የአስፋልት መንገድና ሌሎች ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማይሆኑ ስፍራዎች ላይ ለመጫወት ይገደዳሉ ብለዋል።
መንግስት የዜጎችን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች 34 ሺህ 694 የነበረ ሲሆን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ 35 ሺህ 953 ከፍ ማለቱን ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ የስፖርታዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ቁጥር ወደ 37 ሺህ 078 ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተከለሰው የ2016-2018 የመካከለኛ ዘመን የልማት እና የኢንቨስትመንት ዕቅድ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ወደ 50 ሺህ ለማድረስ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
መንግስት በመካከለኛ ዘመን የልማትና የኢንቨስትመንት ዕቅድ ማብቂያ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
መንግስት በአንድ ቀበሌ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ በሚል ሀሳብ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝም ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው ያብራሩት።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በአንድ ቀበሌ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ አንድ የስፖርት ማዘውተሪያ እንዲኖር ውሳኔ ማስተላለፉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ፣ እንዲገነባና እንዲታደስ በስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ይህም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነት ከማሳደግ አኳያ ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማሰራት እያከናወኑ ያለው ተግባር ለክልሎች፣ ተቋማትና ባለሀብቶች አርአያ ሆኗል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የመዲናዋ ወረዳዎች አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የመገንባትና ነባሮቹን የማደስ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በትምህርት ቤቶች፣በመኖሪያ አካባቢዎችና ተቋማት የሚከናወኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
መንግስት በቀጣይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ደረጃቸውንና ጥራታቸውን ተጠብቆ እንዲገነቡ በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።