ኢትዮጵያና ዓለም ባንክ ጋር 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ዓለም ባንክ ጋር 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዓለም ባንክ ጋር 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚውሉ ስድስት ፕሮጀክቶችን ለመተገበር እንደሚውል ተገልጿል፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመውታል፡፡
ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 300 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው በገጠር አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ማሳለጥ ለሚያስችል የመንገድ መሰረት ልማት ግንባታ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
200 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ለማጠናከር እና ለማስፋፋት እንደሚውል በመረጃው ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ከተሰጠው ብድር ውስጥ 340 ሚሊየን የሚሆነው በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮችና እና ከፊል አርብቶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እንደሚውል ተጠቅሷል፡፡
522 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ለማስፋት እና ታዳሽ ሃይል ማመንጨት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመደገፍ እንደሚውል ተጠቅሷል፡፡
ቀሪው 275 ሚሊየን ዶላር የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን እና ተደረሽነትን ለማስፋት እንዲሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።