ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው - ማሞ ምኅረቱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱን ጨምሮ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 

መድረኩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ስትራቴጂክ ተደራሽነት፣ ደኅንነትና ቅልጥፍና በዘርፉ የመጡ ለውጦች ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በማለም ነው። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በዚሁ ጊዜ፤ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ለአካታች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል። 

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ለአካታች የዲጂታል ፋይናንስ ምኅዳር መጎልበት አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ልማት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም አሁን ላይ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የሞባይል ባንኪንግ፣ የኤቲ ኤምና መሰል የዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።

ብሔራዊ ባንክም በቀጣይ ለዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ዕድገት የሚያግዙ ገንቢ ምክረ ኃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም