ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ባለሃብቶችን በመሳብ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ደሴ፤ መጋቢት 27/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል  ለባለሃብቶች  ያሉትን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች በማስተዋወቅ  ፍሰቱን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ባለፉት ስምንት ወራት  ከ251 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል።

ባለሃብቶች ወደ ስራ ሲገቡም ከ315 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ባለሃብቶች ለልማት የሚሆን የቦታ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በተደረገ ጥረትም ቀደም ሲል የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለወሰዱ 176 ባለሃብቶች መሬት እንደተሰጠም አመልክተዋል።

በቀጣይም ባለሃብቶችን  በመሳብ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  ገልጸዋል።


 

የኮምቦልቻ ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ተወካይ አቶ ሀሺም ሰይድ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ወራት  ለ98 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ በመስጠት ወደ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ስራ ሲገቡም ከ35 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርዓያስላሴ የተመራ የፌዴራልና የክልል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በኮምቦልቻ ከተማ የኮምቦልቻ ኢንዲስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴን ሰሞኑን ጎብኝተዋል፡፡

በአማራ ክልል በ2015 የበጀት ዓመት  483 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አራት ሺህ 724 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት ወደ ልማት እንዲገቡ መደረጉን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም