ስታርት አፖችን በተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ለመደገፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016 (ኢዜአ)፦ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን (ስታርት አፖች) በተደራጀ ተቋማዊ አሰራር ለመደገፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተገለጸ።

የስታርት አፕ ኢትዮጵያ ፎረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

በመድረኩም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የግሉ ዘርፍ እንዲሁም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች /ስታርት አፖች/ ተሳትፈዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ ስታራት አፖች በርካታ የአሰራር ማነቆዎች ይገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል።

መንግስት ይህን ታሳቢ በማድረግ አዳዲስ የፖሊሲና ህግ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይ የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ ማነቆዎች ለመቅረፍ በስራ ሂደት የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ መቶ በመቶ ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ተወስኗል ነው ያሉት።

ምርቶቻቸውን በቀላሉ የሚሸጡበት የኢ-ኮሜርስ እድል በመንግስት መመቻቸቱን ጠቅሰው፥ ከመስሪያ ቦታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን በተደራጀ አግባብ ለመመለስ ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት ስታርት አፖችን በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አይተኬ ሚና እንዳላቸው በሚገባ የተገነዘበ የአሰራር ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለስታርት አፖች የሚሆን ግልጽ የፖሊሲ እና የፋይናንስ ድጋፋ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ይህ ለዘርፉ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሀሳባቸውን ወደ ውጤት ቀይረው በሂደትም የአገር ኢኮኖሚ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ፣ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዲጅታል ዘርፍ ላይ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ተቋማት በተቀናጀ መንገድ ስታርት አፖችን እንዲደግፉ የተቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫም ችግሮችን በአንድ ጊዜ መፍታት እና መቀየር የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ አቅም ያላቸው ወጣቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ከኢትዮጵያ ባለፈ የዓለምን ችግር የሚፈቱ መሆናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻር ለስታርት አፕ ማጎልበቻ የወጣው ፖሊሲ ወጣቶችን በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ፥ ስታርት አፕ እና ካፒታል ገበያ ከፍተኛ ትስስር እንዳላቸው አስረድተዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ስታርት አፖችን የሚያበረታታ እና ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

ፖሊሲው ብዙ ህልም ላላቸው ስታርት አፖች ትልቅ የምስራች ይዞ የመጣ መሆኑንም ተናግረዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም