ቀጥታ፡

በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በሕዝበ ውሳኔ ብቻ ነው - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት በሕዝበ ውሳኔ ብቻ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በስድስቱ ዓመታት የለውጥ ስራዎች፣ በሰላምና የሕግ ማስከበር እርምጃዎች እንዲሁም በበጋ ልማት ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የትግራይ ክልል ወደ ተሟላ የሰላም ሁኔታ እንዲመለስ ስምምነቱን የተሻገሩ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጸዋል።

ይህም ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሰላም እንዲጸና ሁሉንም አይነት ጥረቶችና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ይሁንና ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው ከመሆኑ ባለፈ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል።

የሚነሱ ጥያቄዎችና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይትና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በኃይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ ካለፈው ስህተት አለመማርን ያመለክታል ነው ያሉት።

ይህ አይነት አካሄድ በአሁኑ ወቅት ሰላሙን እያጸና የሚገኘውን የትግራይ ክልል ሕዝብ ለሌላ ዙር ስቃይና እንግልት የሚዳርግ እንዲሁም በክልሉና በአጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም የሚያደበዝዝ መሆኑን አመልክተዋል።

የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን በተመለከተ ያለው አቋም የማይዋዥቅና የጸና ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተቀመጠው አቅጣጫ ብቻና በተጀመረው መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ሌላውን ጊዜና ጉልበት ለልማት ማዋል እንደሚገባና የክረምት ወቅት እየመጣ በመሆኑ ሕዝቡን ለቀጣይ የመኸር አዝመራ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የፌደራል መንግስት የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንደሚፈቱ ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጡንና ከዚህ ውጪ ያለው አካሄድ ለጊዜው ትርፍ የሚያስገኝ ቢመስልም ዘላቂነት አይኖረውም ብለዋል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከፌደራል መንግስት እንዲሁም ከትግራይና አማራ ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችን የያዘ አብይ ኮሚቴ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

የወሰንና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የፌደራል መንግስት ማለትም የመከላከያ ሰራዊት የአካባቢዎቹን ሰላምና ደህንነት ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በትብብር እንደሚቆጣጠርና እንደሚጠብቅ አመልክተዋል።

ተፈናቃዮች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ቀዬያቸው መመለስና በአካባቢው ሕዝብ ምርጫ የአካባቢ አስተዳደሮች መመስረት እንደሚኖርባቸው ነው ዶክተር ለገሰ ያብራሩት።

ሁኔታዎች ሲረጋጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኝነት ሕዝበ ውሳኔውን እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

ሁለቱም ክልሎች ይሄንን አቅጣጫ አክብረው በአካባቢው ላለው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ክልሎቹ በመግለጫዎች እርስ በእርስ ከመወቃቀስ ይልቅ መታረም ያለባቸው ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይትና በድርድር በአብይ ኮሚቴው እየታገዙ መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የፌደራል መንግስት ለተቀመጡት አቅጣጫዎች ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች ሰላምና መረጋጋት እንዳይመጣ ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ሃይሎች የዘረጉትን ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ንግድ ኔትወርክ ለመቆጣጠር ክልሎቹ በጋራ መስራት እንደሚኖርባቸውም ነው ዶክተር ለገሰ የገለጹት።

ችግሩ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው ሕብረተሰቡና ሌሎች አካላት ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም