ቀጥታ፡

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ ሰባት ዞኖች በሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ወኪሎችን መረጡ

ጅማ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፉት አስር ቀናት በጅማ ከተማ ከምዕራብ ኦሮሚያ 7 ዞኖች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ማድረጉን አስታወቀ።

ወኪሎቻቸውን የመረጡት የምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ ጅማ፣ ቡኖ በደሌ እና ከኢሉአባቦራ ዞኖች ከ114 ወረዳዎች በምክክር ሂደቱ ከተሳተፉ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።

ዛሬ በመዝጊያ መርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ፣ ኮሚሽኑ በሀገራችን ያሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም ያሉ ጥያቄዎችን እና አጀንዳዎችን ለምክክር እና ለውይይት በማቅረብ እና በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በማምጣት ረገድ የሁላችንም ተሳትፎ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሁሉም ለምክክሩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።


 

የኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታና የምክክር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ በበኩላቸው የሚደረገው ምክክርና ውይይት ግልጽና ሁሉንም ለማካተት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ የተወካዮች ልየታ መርሃ-ግብር ላይ ከምዕራብ ኦሮሚያ የተውጣጡ ከየወረዳው አስር አስር የህብረተሰብ ክፍሎች ቀርበዋል ብለዋል።

ከእነዚህም መካከል ሁለት ሁለት ተወካዮች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ በማቅረብ የሚሳተፋ ተወካዮች መለየታቸውን ገልጸዋል።

ከቄለም ወለጋ በምክክሩ ከተሳተፉት መካከል የሀይማኖት አባት ጌታቸው ከበደ ጊዜው ችግሮቻችንን በመነጋገርና በመወያየት ለመፍታ የሚስፈልግበት በመሆኑ ለምክክሩ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ለህዝባችን አንድነትና ለሀገር ሰላም ሲባል በመመካከር ችግሮችን መለየት ብሎም ያላግባቡን ነጥቦችን ለይተን መፍትሄ መስጠት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የቄለም ወለጋ ዞን ተሳታፊ ወይዘሮ ናፍቆት ዲባባ፣ የህብረተሰቡን ሀሳብ በመያዝ በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን ለመምረጥ እንደተገኙ ገልጸው ምክክሩ ፍሬያማ ሆኖ ሰላማችን እንዲሰፍን ምኞቴ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም