በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው -- የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው -- የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን
አዳማ፣መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎ እንዲጎላ ሴቶችን የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው።
በምክክሩ ሴቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች ትልቅ ትኩረት እንዲያገኙ የምክክሩ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን በሂደቱ የተለያየ ሚና እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማና የምክክሩ ሂደት ላይ በየደረጃው ያሉ የሴቶች አደረጃጀቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማስገንዘብ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ በየደረጃው የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በተለይ በኦሮሚያ፣ በሐረር፣ በድሬ ደዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌና በሌሎች ክልሎች የኢትዮጵያ ሴቶች አደረጃጀቶች ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ሂደቱ ሴቶች በአወያይ እንዲሳተፉ በየደረጃው ካሉ የፌዴሬሽኑ አባላት ተመርጠው ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን የገለጹት ወይዘሮ አስካለ የሴቶች አጀንዳ እንዲጎላ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ውጤት እጅጉን ተጠቃሚ የሚሆኑ ሴቶች በመሆናቸው ከሂደቱ ጀምሮ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እፀገነት ሃይሌ በበኩላቸው በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች አጀንዳ እንዲደመጥ የክልሉን የሴቶች አደረጃጀቶች በ7 ክላስተር በማደራጀት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።
ተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎችን የመለየት ሂደትም ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኢፍቱ አባስ እንዲሁ በግጭቶችና አለመግባባቶች ውስጥ የበለጠ ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በምክክሩ ሂደት በንቃት በመሳተፍ አጀንዳችንን ማስያዝ አለብን ብለዋል።
በተለይ ሴቶች የሀገራዊ ምክክሩን ዓላማና ግብ በአግባቡ እንዲገነዘቡና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በአስተዳደሩ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።