ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚያመጣውን የቱሪዝም አማራጮችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆን አለባቸው

አሶሳ፣መጋቢት 26 / 2016 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ሆቴሎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያመጣውን የቱሪዝም አማራጮች በሚገባ ለመጠቀም ከወዲሁ ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስገነዘበ።

በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎችን ማነቃቃት ዓላማው ያደረገ ውይይት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡


 

የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሞሲሳ መሸሻ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ የቱሪዝም አማራጭ ይዞ እየመጣ ነው፡፡

ይህም ክልሉን በተለይም አሶሳ ከተማን የቱሪዝም ማዕከል እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

አሁን በከተማው ያለው የሆቴሎች ቁጥርና ደረጃ እድሉን ተጠቅሞ ዘርፉ ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማምጣት የሚያስችልነው ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል፡፡

በሆቴል የአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ እና ሌሎች ባለሃብቶች ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ በማካሄድ፣ ባለሙያ በማሟላት፣ ጥራት ያለው የሆቴል አገልግሎት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አቶ ሞሲሳ አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለሆቴሎች ስልጠና ከማዘጋጀትና አቅማቸውን ከማጎልበት ጀምሮ ለቱሪዝም መሻሻል ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እና ሌሎች ጉዳዮችን ለማስፋፋት እና ለማሟላት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ነክ ተቋማት ባለሙያ አቶ አየለ ጅራታ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ ሆቴሎች በዘርፉ  አገልግሎት መስጠት ላይ ያለባቸውን ክፍተት በሚገባ ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአገልግሎት ዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለመንግስት አሳውቀው በትብብር ለመስራት የሚያስችል ሁኔታን ማመቻቸትም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ከፍያለው አድነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለሆቴል ቱሪዝም የሚፈጥራቸው አማራጮችን ለመጠቀም እኛም ለህብረተሰቡ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የመስጠት ግዴታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በዚህ ረገድ "የሆቴሎችን አቅም ለማሳደግም ስልጠናና እና መሰል እገዛዎችን ከመንግስት እንጠብቃለን" በማለት ገልጸዋል።

የሆቴሎችን አገልግሎት ለማሳደግ ጉዳዮ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ቋሚ ክትትል እና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የጠቆሙት ሌላኛው ተሳታፊ አቶ አብደላ ሰይድ፤ በከተሞች ውሃ እና መንገድን ማሻሻል የመንግስት ወሳኝ ድርሻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሆቴሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን የማሻሻል ተግባር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ሁለት ባለ አንድ፣ አንድ ባለ ሁለት ኮከብ ሆቴሎች እና ከ350 በላይ ሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሚገኙም ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም