ቀጥታ፡

የፊቼ ጨምበላላ በዓል በውስጡ የያዛቸው እሴቶችን ይበልጥ በማንጸባረቅ ይከበራል

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 26/2016(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል በውስጡ የያዛቸውን የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እሴቶችን ይበልጥ በሚያንጸባርቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

ፊቼ ጨምበላላ በዓልን ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ  እንግዶች ወደ ሀዋሳ መግባት መጀመራቸውም ተመላክቷል።

የቢሮው ሀላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ለበዓሉ ዝግጅት ስድስት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ከአንድ ወር በላይ ሲሰሩ ቆይተዋል።

የዘንድሮው የፊቼ ጨምበላላ በዓል በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በስነጽሁፍና ባህል፣ በሲምፖዚየምና በሌሎች ክዋኔዎች እየተከበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የበዓሉ ዋዜማ የፊጣራ ቀን በሀዋሳ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የሀገር ውስጥና የውጪ እንግዶች በተገኙበት እንደሚከበር ገልጸዋል።

የፊቼ ጨምበላላ በዓል በውስጡ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እሴቶችን የያዘ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወሰንየለህ በሲምፖዚየሙ እነዚህን እሴቶች የሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች እንደሚከወኑ ተናግረዋል።

ቅዳሜ በሀዋሳ ጉዱማሌ ሶሬሳ አደባባይ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ የሲዳማ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በብሔሩ ባህላዊ ክዋኔ በቄጣላ ስነ-ስርዓት አዲሱን አመት እንደሚቀበሉና በልዩ ሁኔታ እንደሚያከብሩት አቶ ወሰንየለህ ገልጸዋል።

ለበዓሉ ከሀገር ውስጥና ከውጪ በርካታ እንግዶች ወደ ሀዋሳ ስለሚመጡ በከተማው የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደወትሮው አገልግሎታቸውን ሳያስተጓጉሉ እንግዶችን እንዲያስተናግዱ ጥሪ አቅርበዋል።

የፊቼ ጨምበላላ በዓል ነገና ከነገ ወዲያ በሀዋሳ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር በመግለጫው ተጠቅሷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም